ከአሜሪካ የሚመጡ ስፔሻሊስት ሃኪሞች በአዲስ አበባ ነፃ ህክምና ሊሰጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከአሜሪካ የሚመጡ ስፔሻሊስት ሃኪሞች በአዲስ አበባ ነፃ ህክምና ሊሰጡ ነው
አዲስ አበባ ጥር 5/2012(ኢዜአ) ከአሜሪካን የሚመጡ ስፔሻሊስት ሃኪሞች ከመጪው ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የነፃ ህክምና አገልግሎት ሊሰጡ ነው። ስፔሻሊስት ሃኪሞቹ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር የነፃ ህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ነው። የህክምና ልኡኩ ከፊታችን ሰኞ እለት ጀምሮ ለተከታታይ 5 ቀናት በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የነፃ ህክምና አገልግሎት ይሰጣል። ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ አንብሬ ለኢዜአ እንድገለጹት ስፔሻሊስት ሃኪሞቹ በሚኖራቸው ቆይታ ለአዋቂዎች የውስጥ ድዌ ህክምና፤ አጠቃላይ የህጻናት ህክምና የጥርስና የህብለሰረሰር ህክምና አገልግሎት የሚሰጡ የሆናል። ሆስፒታሉ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ2 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች በተለያዩ ህክምና አይነቶች የነጻ ህክምና አገልግሎት መስጠቱንም አስታውሰዋል። የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቀደም ሲል የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ከነበረው የቲቢና ሌሎች የመተንፈሻ አካላት ህክምና በተጨማሪ ስድስት አዳዲስ የህክምና አገልግሎቶችን መስጠት መጀመሩንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ከህንድ የመጡ 14 ዶክተሮችም በቅዱስ ጳውሎስ ሚኒሊዬም ሜዲካል ኮሌጅና በአቤት አጠቃላይ ሆስፒታል ነፃ የህክምና አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።