ቀጥታ፡

የጤና ሚኒስቴር በቲቢና ሌሎች የመተንፈሻ አካላት ሕመሞች ላይ ጥናት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4/2012 (ኢዜአ) የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ጋር በመተባበር በቲቢና ሌሎች የመተንፈሻ አካላት ሕመሞች ላይ ጥናቶችን እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ። የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ከሳንባ በሽታዎችና ሌሎች ፅኑ ህመሞች ጋር ተያይዞ በሚከሰቱ ህመሞች ዙሪያ የሚሰራ ማህበራዊ ተቋም ነው። በመሆኑም ቶራሲክ ሶሳይቲ በቲቢ፣ መድኃኒት በተለማመደ ቲቢና በመተንፈሻ አካላት ሕመሞች ላይ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን በሚኒስቴሩ የቲቢና የሥጋ ደዌ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ታዬ ለታ ገልጸዋል። በተለይ ቲቢ ህመም ላይ በትኩረት እየሰራ በመሆኑ ሚኒስቴሩ ስልጠናዎችን በመስጠት ድጋፍ እያደረገለት መሆኑን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ቴዎድሮስ ኃይሌ እንደሚሉት ሶሳይቲው የሳንባ፣ የአስም እንዲሁም ሥር የሰደዱ የመተንፈሻ አከላት ሕመሞችን በዛለቂነት ለመከላከል በትኩረት እየሰራ ነው። በነገው እለት በአዲስ አበባ ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚካሄደው ጉባዔም በቲቢ፣ አስምና ስር በሰደዱ የመተንፈሻ አካላት ጽኑ ሕሞሞች ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል። በመድረኩ ላይ የቲቢ፣ አስም፣ ሥር የሰደደ የመተንፈሻ አካላት ችግር፣ የሳንባ ካንስርና ተያያዥ የጤና ጎዳዮች ላይ ጥናቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግም ታውቋል። ጥናቱን ተከትሎ ከዘርፉ ባለሙያዎችና ከባለድርሻ አካላት በሚነሱ ሀሳቦች ለጥናቱ ማዳበሪያ የሚሆኑ ግብቶች ይገኛሉ ተብሎም ይጠበቃል። ጉባኤው "በኢትዮጵያ ውስጥ በሳንባ ሕክምና ላይ ጥናቶችን በማድርግ ያሉትን የጤና ችግሮች ማሻሽል" በሚል መሪ ሐሳብ ይካሄዳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም