በአሜሪካ በተቃውሞ ሰልፍ የሚታወቁ ኢትዮጵያውያን ለድጋፍ ሰልፍ ወጡ - ኢዜአ አማርኛ
በአሜሪካ በተቃውሞ ሰልፍ የሚታወቁ ኢትዮጵያውያን ለድጋፍ ሰልፍ ወጡ
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2010 የኢትዮጵያን መንግስት በመቃወም በአሜሪካ ተደጋጋሚ ሠልፍ በማድረግ የሚታወቁ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን በመደገፍ ሰልፍ ወጡ። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በአሜሪካ ርዕሰ-መዲና ዋሽንግተን ስቴት ዲፓርትመንት በራፍ ላይ ነው በዶክተር ዐቢይ ፎቶ ያሸበረቁ አልባሳትን በመልበስ "ስንደመር ያምርብናል" እና ሌሎች የድጋፍ መፈከሮችን በማንገብ የተሰለፉት። በሰልፉ ላይ የአንድ ወር መንታ ህጻናትን ይዛ የወጣች ኢትዮጵያዊትን ጨምሮ ሌሎች ኢትዮጵያንና ኤርትራውያን የዶክተር ዐቢይን አመራር ደግፈው ከሰልፉ ጋር መደመራቸው የድጋፍ ሰልፉ ደማቅ ገጽታ ነበር። https://youtu.be/r0jt5PwmCEs በዕለቱ በስፍራው የተገኘው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን/ኢሳት ጋዜጠኛ መሳይ መኮንንም የራሱን ስሜት ይገልጻል። https://youtu.be/W8YoUT2wlMg ሰልፈኞቹ ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ በነበረው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በደረሰው ፍንዳታ ለተጎዱ ሰዎች ማዘናቸውንና የድርጊቱ ተሳታፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል። የሰልፍ ግብረ-ኃይሉ በስቴስ ዲፓርትመንት የአፍሪካ ዴስክ በመግባት የአሜሪካ መንግስት ለዶክተር ዐቢይ ያለውን አድናቆትና ድጋፍ እንዲሁም የአሜሪካ መንግስት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን እንዲቆም የሚጎተጉት መልዕክት አስገብቷል።