ቀጥታ፡

ዲቢኤል ግሩፕ በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመድሐኒት ፋብሪካ ሊከፍት ነው

አዲስ አበባ የካቲት 4/2012 (ኢዜአ) የባንግላዴሹ ኩባንያ ዲቢኤል ግሩፕ በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመድሐኒት ፋብሪካ ለመክፈት በሂደት ላይ እንደሆነ በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ አምባሳደር ሞኒሩል ኢስላም ገለጹ። የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሁለት ወር በኋላ በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት የሁለትዮሽ ስምምነት እንደሚፈራረሙም አስታውቀዋል። በ100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ2010 ዓ.ም ተመርቆ ስራ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፤ የተለያዩ ኩባንያዎችም በፓርኩ የተዘጋጁ ሼዶችን ወስደው ወደ ስራ ገብተዋል። በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ አምባሳደር ሞኒሩል ኢስላም የአገራቸው ኩባንያ ዲቢኤል ግሩፕ በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ መሰማራቱን አውስተዋል። ኩባንያው ምርቶቹን ወደ አውሮፓና አሜሪካ እየላከ መሆኑንና ለኢትዮጵያዊያንም የስራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል። አምባሳደሩ ዲቢኤል ግሩፕ ከጨርቃጨርቅና አልባሳት በተጨማሪ በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመድሐኒት ፋብሪካ ለመክፈት በሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል። በኢትዮጵያ የመድሐኒት ማምረቻ ኢንዱስትሪ እምቅ የሚባል አቅም ያለው ዘርፍ በመሆኑ ኩባንያው በኢንዱስትሪ ፓርኩ ፋብሪካውን ለመክፈት መወሰኑንም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ 10 የሚሆኑ የባንግላዴሽ ኩባንያዎች እንደሚገኙና መቀሌን ጨምሮ በሀዋሳና በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶች መሰማራቸውን ጠቅሰዋል። ባንግላዴሽ በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የቴክኒክ ባለሙያዎችን በመመደብ ለኢትዮጵያዊያን የጨርቃጨርቅና አልባሳት አመራረት የቴክኒክ ሂደቶችን በተመለከተ ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። ከምርት ባለፈ የገበያ አማራጮችን በማፈላለግ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም እንዲሁ። ባንግላዴሽ ከቻይና በመቀጠል የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርት የኤክስፖርት ገቢ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። አምባሳደር ሞኒሩል በኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ በማደግ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ባንግላዴሽ ተሞክሮዋን ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል። ከጨርቃጨርቅና አልባሳት በተጨማሪ የባንግላዴሽ ኩባንያዎች በቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም በፕላስቲክ ምርት የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸውና የገበያ አማራጮችን እየተመለከቱ መሆኑንም አብራርተዋል። የኢትዮጵያ የቆዳ ሀብት ሰፊ በመሆኑ የባንግላዴሽ ኩባንያዎች በዘርፉ ቢሰማሩ መልካም ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል። የኢትዮጵያና ባንግላዴሽን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር በቅርቡ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በየአገራቱ ጉብኝት እያደረጉ እንደሆነም አክለዋል። የባንግላዴሽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቡል ካላም አብዱል ሞመን በሚያዚያ 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉም አምባሳደር ሞኒሩል ጠቁመዋል። በጉብኝታቸው ወቅትም ኢትዮጵያና ባንግላዴሽ በነጻ ቪዛ፣ በባህል፣ በኢንቨስትመንትና ሌሎችም መስኮች በትብብር መስራት የሚያስችሏቸውን ስምምነቶች እንደሚፈራረሙ ተናግረዋል። ባንግላዴሽ በትምህርት፣ በባህል፣ በህክምና፣ በምህንድስናና በስፖርት መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር አዲስ ትብብር ለመፍጠር ፍላጎት አላት ብለዋል አምባሳደር ሞኒሩል። 'ኢትዮጵያና ባንግላዴሽ በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ናቸው' ያሉት አምባሳደሩ ልምዶቻቸውን በመለዋወጥ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል። ባንግላዴሽ ኤምባሲዋን እ.አ.አ በ2016 በኢትዮጵያ የከፈተች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ከአገሪቷ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሕንድ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል ታከናውናለች። ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችና ስጋ ወደ ባንግላዴሽ ስትልክ የቡና ማሸጊያዎች፣ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶችን ደግሞ ከዚያ ታስገባለች።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም