ቀጥታ፡

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ምርታማነትን እያሳደገ ነው

ነገሌ፣ የካቲት 4/2012 (ኢዜአ) ተፋሰስን መሰረት በማድረግ የተካሄደው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ስራ ምርታማነታቸውን እያሳደገው መሆኑን በጉጂ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ  በ2011/2012 የመኸር ወቅት ምርት እንዲጨምር አስተዋጽኦ ማድረጉን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡ አቶ ፍቅሬ ገናሌ በዞኑ የቦሬ ወረዳ አርሶ አደር ሲሆኑ ከዚህ በፊት ለማገዶና ጣውላ ፍጆታ ደን እየተጨፈጨፍ አፈሩ በጎርፍ  በመሸርሸሩ አካባቢያቸው ተራቁቶ እንደነበር ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡ በዚህም የመሬቱ ለምነት  በመቀነሱ ምርት መስጠት ተስኖት ከበልግም ሆነ ከመኸር አዝመራ የሚያገኙት ምርት ከእጅ ወደ አፍ ብቻ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የጀመሩት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ የአፈሩ ለምነት እየተመለሰ በመምጣቱ ምርታማነታቸው ለማሳደግ እንዳገዛቸው  ገልጸዋል። በተለይ ባለፈው የመኸር ወቅት በሄክታር 18 ኩንታል የገብስ ምርት መሰብሰባቸውን ጠቅሰው ይህም ከቀዳሚው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር በስድስት ኩንታል ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል። የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ሂርባዬ ሮቤም ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና ድርቅ የአካባቢያቸው መገለጫዎች እንደነበሩ አውስተዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት ባከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ችግሩን መቀነስ በመቻላቸው አካባቢያቸው ወደ አረንጓዴነት መቀየሩን አመልክተዋል። በዚህም  ከዓመት ዓመት የእንስሳት መኖና የመጠጥ ውሃ  በአቅራቢያቸው ለማገኘት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ጠቅሰዋል፡፡ የሰበል ልማታቸውን ለማሳደግ እንደረዳቸው ገልጸው ባለፈው የመኸር ወቅት ካለሙት መሬት አዝመራው ተጠቃሎ ሲገባ  በሄክታር 60 ኩንታል የስንዴ  ምርት  አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። ዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ዘወዴ በቀለ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ የመኸሩ ወቅት ምርት እንዲጨምር አድርጓል። በ2011/2012 የመኸር ወቅት 170 ሺህ 953 ሄክታር መሬት ላይ በዋናነት ስንዴ፣ ገብስና ጤፍ መልማቱን አቶ በቀለ ተናግረዋል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም