ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 2 ዓመታት የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን እድል አላት

አዲስ አበባ፣ የካቲታ 4/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የምትሆንበት እድል መኖሩን የዓለም ንግድ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር አለን ወልፍ ገለጹ። ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ለበርካታ ዓመታት ጥያቄ ብታቀርብም አስካሁን ሊሳካላት ሳይችል ቀርቷል። ሆኖም ጥያቄውን እውን ለማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚመራ ዓለም አቀፍ ተደራዳሪ የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ እንቅስቃሴ ጀምሯል። የንግድ ህጉን ጨምሮ የሚደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በር ይከፍታሉ። የዓለም የንግድ ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር አለን ወልፍ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ 22 የዓለም ሀገራት የድርጅቱ አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርበዋል። በአፍሪካ የአባልነት ጥያቄ ካቀረቡ ዘጠኝ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ሳኦቶሚና ፕሪንሲፒ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነትን አፅድቀዋል። ይህም የአህጉሪቱን የንግድ ትስስር ከማጎልበት ባለፈ ለዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት እንደሚያግዝ ይታመናል። ኢትዮጵያ ስምምነቱን ከማፅደቅም ባለፈ የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እያደረገች ትገኛለች። የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ሀገራዊ ኢኮኖሚውን ከማነቃቃትም ባለፈ የድርጅቱ አባል ሀገራትን የመቀላቀል እድል የሚፈጥርላት መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ሀገር ትሆናለች የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። የድርጅቱ አባል መሆን ጥራት ያላቸውና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ምርቶችን ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚያስችል መድረክ ይፈጥራልም ነው ያሉት። የኢፌዴሪ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እያደረገች መሆኗን ገልጸዋል። እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ስኳር ፕሮጀክት፤ ኤሌክትሪክ፤ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ሌሎችም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል የሚዘዋወሩበት አሰራር እተዘጋጀ መሆኑንም አብራርተዋል። "ከዓለም የንግድ ድርጅት ጋር የሚደረገው ድርድር በመልካም ሂደት ላይ ነው ያሉት አቶ መላኩ፤ በቅርቡም ጥያቄያችን እውን ይሆናል" ብለዋል። የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ከኤርትራ ውጭ ሁሉም የፈረሙት ሲሆን 28 አገራት ደግሞ አፅድቀውታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም