ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከኢትዮጵያዊያን ጋር ይወያያሉ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 4/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከ15 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ጋር ውይይት ያደርጋሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከነገ ጀምሮ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለሶስት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት የሚያደርጉ ሲሆን በዚያው ከሚኖሩ ከ15 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ጋርም ውይይት ያደርጋሉ። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን የዶክተር ዐቢይ አህመድ ጉብኝትን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የመደመር ፍልስፍና በተለይ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ዙሪያ ትኩረት ማድረጉን ተከትሎ እስካሁን ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች ከተለያዩ አገራት ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በሳዑዲ አረቢያ፣ ግብጽ፣ ሱዳንና ሌሎች አገራት ቀደም ሲል ባደረጉት ጉብኝት በአገራቱ በእስር ላይ የነበሩ ዜጎች ከእስር ተፈተው እንዲመለሱ ማድረጋቸውም ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚያደርጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከ15 ሺህ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ አቶ ንጉሱ ተናግረዋል። በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከሚኖሩና ከመካከለኛው ምስራቅ ከመጡ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውይይት እንደሚያደርጉ ነው አቶ ንጉሱ የገለጹት። የኢትዮጵያ መንግስት በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ዜጎች መብታቸው እንዲከበር የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል። በአገር ውስጥ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ጀምሮ በሚኖሩበት አገር የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ይናገራሉ። በተጨማሪም ዜጎች ለሥራ ስምሪት በህጋዊነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ ከዮርዳኖስ፣ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሥራ ስምሪት ስምምነት መፈራረሙን አስታውሰዋል። ዜጎች ክብራቸውና መብታቸው እንዲጠበቅ በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም