ቀጥታ፡

የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ከድህነት መውጫ መንገድ ነው

መቀሌ፤ የካቲት 4/2012( ኢዜአ) የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ከድህነት መውጫ መንገድ መሆኑን የትግራይ ክልል ግብርና ና ገጠር ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገቡ ገለጹ።

በትግራይ ክልል በየዓመቱ የሚካሄደው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ  በክልሉ ደቡባዊ ዞን ኦፍላ ወረዳ ሓሸንገ ተፋሰስ ላይ በይፋ ተጀምሯል።

በዘመቻ መልክ የሚካሔደው  ስራው የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገቡና የዞኑ አስተዳደሪ አቶ ረዳኢ ሓለፎም አስጀምረውታል።

የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገቡ በስነ ስርአቱ ላይ እንደገለጹት ክልሉ ለበርካታ አመታት ባከሄደው የአካባቢ ጥበቃ ስራ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ እንድትሆን አስችሏታል ።

በክልሉ ባለፉት አመታት በተሰሩት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ተጎድተው የነበሩ አከባቢዎች መልሰው  አገግመዋል።

የአካባቢ ጥበቃ ስራው የተፈጥሮ ሚዛን እንዳይዛባ የሚከላከል ከመሆኑ በተጨማሪ  ለመስኖ ልማትና ለንብ እርባታ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መምጣቱን የቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።

የአፈርና ውሀ ጥበቃ በተሰራባቸው አካባቢዎች በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች በንብ ማነብ፣በመስኖና በእንስሳት እርባታ ላይ ኑሮቸውን እንደመሰረቱ አስረድተዋል ።

 የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ የድህነት መውጫ መንገድ በመሆኑ  ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

በክልሉ ለሀያ ቀናት በሚካሄደው ነጻ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ዘመቻ ከ1ነጥብ2 ሚልዮን በላይ ህዝብ  የሚሳተፍ ሲሆን 70 ሺህ ሄክታር መሬት በሚሸፍኑ ተፋሳሶች ላይ የተለያዩ እርከኖች ይሰራሉ ።

የትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ረዳኢ ሓለፎም በስነ ስርአቱ ላይ እንዳሉት የዓመቱ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ዘመቻ በተፋሰሱ ላይ የተለያዩ እርከኖችን በመገንባት ወደ አሸንጌ ሀይቅ የሚገባ ደለል መከላከል በሚያስችል መልኩ ይከናወናል።

የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ የአንድ ወቅት ስራ ዘመቻ ሳይሆን የዘወትር ስራ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቶ ረዳኢ ተናግረዋል።

በስራው ላይ ተሳታፊ የነበሩ የመንከረ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር አድማሱ አማረ እንዳሉት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ለእርሻ ስራቸው የህልውናችን መሰረት በመሆኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የአካባቢው አርሶ አደሮች የእርሻ መሬታቸው በጎርፍ እንዳይወሰድ የሚከላከልና ምርታማነት እንዲጨምር የሚያደርግ በመሆኑ ቀስቃሽ ሳያስፈልጋቸው በነቂስ ወጥተው በዘመቻው እየተሳተፉ መሆናቸውን ነው         አቶ አድማሱ የተናገሩት።

በሓሸንገ ተፋሰስ መንከረ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የተጀመረው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ዘመቻ በጀነራል ሰዓረ መኮንን ስም ተሰይሟል።

         
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም