ቀጥታ፡

"ኢትዮጵያዊያን ኤርትራን ለመጎብኘት ተዘጋጁ፤ ኤርትራዊያንም አገራችሁን መጥታችሁ ጎብኙ" - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ  ሰኔ 20/2010 "ኢትዮጵያዊያን ኤርትራን ለመጎብኘት ተዘጋጁ፤ ኤርትራዊያንም በፍጥነት አገራችሁን መጥታችሁ ጎብኙ" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ  ። ይህንን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኤርትራ መንግስት ልዑካን ትናንት ምሽት በብሔራዊ ቤተ-መንግስት የእራት ግብዣ ባደረጉበት ወቅት ነው። በወቅቱ ባደረጉት ንግግርም፤ "የሁለቱ አገራት ህዝቦች ፍቅር ተጠምተው ለዓመታት ቆይተዋል" አርቲስቶች አዲስ አመትን በጋራ ለማክበር  እንዲዘጋጁና የኢትዮጵያ አየር መንገድም በረራ እንደሚጀምር ጠቁመዋል። የሚያዋጣው ብቸኛ አማራጭ ፍቅር ብቻ በመሆኑ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ሰላም የመፍጠር ፍላጎት እንዳላት አስታውቀዋል። ከኤርትራ ጋር የተገኘው ስምምነት ኢትዮጵያዊያን የጀመሩት የፍቅር፣ የሰላምና የይቅርታ ግስጋሴ ውጤት ያመጣው በመሆኑ ለዚሁ ዓላማ የተባበራችሁ ኢትዮጵያዊያንን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳልህ በበኩላቸው ለተደረገው ደማቅ አቀባበል አመስግነው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን የመደመር ሃሳብ እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለው ልዩነት ተዘግቶ አዲስ ምዕራፍ መከፈቱንም ጭምር ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት። በእራት ግብዣው ላይ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ አማካሪና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የማነ ገብረአብ እና የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ኦስማን ሳለህን ጨምሮ የኃይማኖት አባቶች፣ አትሌቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ሌሎችም ተጋባዥ ግለሰቦች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም