በተሽከርካሪ አደጋ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ

75
የካቲት 3/2012 (ኢዜአ)  በምስራቅ ጎጃም ዞን የጁቤ ወረዳ ዛሬ ከቀኑ 7 ሰዓት አካባቢ በደረሰ የትራፊክ አደጋ 4 ሰዎች ወዲያውኑ ሲሞቱ በ24 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን የዞኑ ፖሊስ ገለፀ ። በምስራቅ ጎጃም ፖሊስ መምሪያ የመንገድ ትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጎበዜ ይርሳው እንደገለፁት አደጋው የደረሰው ከባሶ ሊበን ከተማ 28 ሰዎችን አሳፍሮ ወደ ኮርክ ከተማ በመጓዝ ላይ የነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አማ 01594 አይሱዙ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በመገልበጡ ነው ። አደጋው የደረሰው ልምጭም በተባለው ቀበሌ ሲሆን 4 ሰዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ በ9 ሰዎች ከባድ በ15 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ዋና ኢንስፔክተሩ ገልፀዋል ። የሟቾቹ አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው የተሰጠ ሲሆን የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 24 ሰዎች ደግሞ በደብረማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታልና በየጁቤ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በህክምና ላይ ናቸው ተብሏል ። አሽከርካሪው ለጊዜው በመሰወሩ ክትትል እየተደረገ ነው ያሉት ዋና ኢንስፔክተሩ የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑንም ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም