ዩኒቨርሲቲው በሚሰጠው ነጻ የህግ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተጠቃሚዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው በሚሰጠው ነጻ የህግ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተጠቃሚዎች ገለጹ
ጎባ ኢዜአ የካቲት 3/2012 በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ነጻ የህግ ድጋፍ ማዕከል በተሰጣቸው አገልግሎት አለአግባብ የተነፈጉ መብቶቻቸውን ማግኘት እንደቻሉ በአካባቢው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተጠቃሚዎች ገለጹ። የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በሮቤ ከተማ ባቋቋመው ነጻ የህግ ድጋፍ ማዕከል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወጣት ተሾመ ከበደ አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ እንዳለው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት ጋር በተያየዘ በደረሰበት የአካል ጉዳት በአቅም ማነስ ምክንያት ጠበቃ አቁሞ መከራከር ባለመቻሉ ፍትህ አጥቶ መቆየቱን አስታውሷል፡፡ "አሁን ግን ከመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ባገኘሁት ነጻ የህግ አገልግሎት በባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት 80 ሺህ ብር የካሳ ክፍያ እንዲከፈለኝ ተወስኖልኛል" ብሏል፡፡ እንደ ወጣት ተሾመ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው በሚሰጠው ነጻ የህግ አገልግሎት የሱን ጨምሮ ብዙ አቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች ፍትህ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ በነበራቸው የመኖሪያ ቤት ይገባኛል ክርክር በገንዘብ ችግር ምክንያት መፍትሄ ሳያገኝ የቆየውን ጉዳይ ዩኒቨርሲቲው በከፈተው ነጻ የህግ አገልግሎት ማዕከል በኩል የተወሰነላቸውን ቤታቸው ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላዋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ወይዘሮ አለሚቱ ሁንዴ ናቸው፡፡ ነፃ የህግ አገልግሎቱ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎችንም የአካባቢውን አቅመ ደካሞች ፍትህ እንዲያገኙ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም አውስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የህግ ትምህርት ቤቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ተማሪ አኒሳ ሰኢድ "በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ የሚገኘው ነጻ የህግ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ላይ የሚደርሰውን የፍትህ መጓደል ችግር ከማቃለሉም በተጓዳኝ ተማሪዎች የስራውን ዓለም ሲቀላቀሉ አዲስ እንዳይሆንባቸው ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው" ብላለች፡፡ ማህበራቸው በአገልግሎቱ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ ሰለሞን ግርማ በበኩላቸው "ዩኒቨርሲቲው በሴቶች፣ በአካል ጉዳተኞችና አነስተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት በማድረግ ነፃ የህግ አገልግሎት እየሰጠ ነው "ብለዋል። ባለፉት አምስት ወራት 400 ለሚጠጉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ወረዳዎች በከፈተው አምስት ማዕከላት አማካኝነት አገልግሎት መስጠቱን ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ሰለሞን እንዳስረዱት ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠውን ነጻ የህግ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ አዳዲስ ማዕከላትን የመክፈትና የነበሩትን በሰው ኃይል የማጠናከር ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በ2006 ዓ.ም. በሁለት ማዕከላት የጀመረው ነጻ የህግ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ወደ አስር ከፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ከዲኑ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡