የዳያስፖራው ማህበረሰብ የሀገሩን ሰላም ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የዳያስፖራው ማህበረሰብ የሀገሩን ሰላም ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር ተጠየቀ
የካቲት 03 / 2012 ( ኢዜአ ) የዳያስፖራው ማህበረሰብ የአገሩን ሰላም ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ጥሪ አቀረቡ ። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ''ዳያስፖራው ለአገር ሰላም ግንባታ'' በሚል መሪ ሃሳብ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ዳያስፖራው አገሪቷ የተያያዘችውን የለውጥ ጉዞ ለማገዝ አቅሙም እውቀቱም አለው ብለዋል። በመሆኑም ከዚህ ቀደም የነበረውን አስተዋጽኦ በማጠናከር በተለይ ደግሞ ለሰላም የሚያደርገውን አስተዋፆ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል። ''በርካታ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች የሚኖርበት ማህበረሰብ የዴሞክራሲ ባህሉ ያደገ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ ይህ ልምድና ተሞክሮ ለኢትዮጵያም ያስፈልጋል ብለዋል። በኢትዮጵያ በሃሳብ የዳበረ የፖለቲካ ስርዓት እንዲኖርና የሃሳብ ክርክር በስፋት እንዲለመድም ዳያስፖራው የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አብረሃም ስዩም እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት ዳያስፖራው ከአገሩ ሰላም በላይ የሚያሳስበው ጉዳይ የለም። በተለያዩ የኢንቨስትመንትና ሌሎች ዘርፎች ለመሰማራትና ባለሃብቶችን ለመሳብ የአገር ሰላም ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል። የአገርን ሰላም እውን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ "ሁሉም ለሰላም ዘብ ሲቆም" መሆኑን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበርም "ስለ ሰላም የሚሰራ ኮሚቴ" በማቋቋም ለአገር ሰላምና የህዝቦች ደህንነት ይሰራል ብለዋል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የቀድሞው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እሌኒ ገብረመድህን እንዳሉትም ስለ አገር ግንባታ አስተዋጽኦ ሲታሰብ "እኔ ምን ማበርከት እችላለው?" የሚለውን ይዞ መነሳት ያስፈልጋል። በመሆኑም አንድ በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዊ በየትኛውም መስክ አገሩን ሊያግዝ ይገባል ነው ያሉት። የዳያስፖራው ማህበረሰብ ሁል ጊዜ የተመቻቸ ነገርን መጠበቅ ሳይኖርበት በእኔነት ስሜት ለኢትዮጵያ ስኬት ሊሰራ ይገባልም ብለዋል። በውይይቱ ላይ ከተለያዩ የዓለም አገራት የተውጣጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ተሳትፈዋል። ከተሳታፊዎቹ መካከል አስተያየታቸውን የሰጡ የዳያስፖራ አባላት ለአገራቸው ሰላም፣ እድገትና ብልፅግና የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ኢትዮጵያን ለዜጎቿ ምቹና ፍፁም ሰላም የሰፈነባት ለማድረግ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል። በተለያዩ የውጭ አገራት ኑሯቸውን ያደረጉ ከ3 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በውጭ አገራት እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።