ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጎን እንቆማለን - በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን - ኢዜአ አማርኛ
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጎን እንቆማለን - በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2010 ኢትዮጵያን ወደ መደመር እያሸጋገረ ካለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አመራር ጎን እንቆማለን ሲሉ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ተናገሩ። ኢትዮጵያዊያኑና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያኑ "የትውልድ ድልድይ" በሚል ርዕስ በዋሽንግተን ዲሲ ባካሄዱት ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ እየወሰዷቸው ባሉት የፖለቲካና ምጣኔ ኃብታዊ እርምጃዎች እና በተመዘገቡት ለውጦች ዙሪያ ተነጋግረዋል። በውይይቱ ላለፉት በርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ትችቶችን ያዘሉ ጽሁፎች በማቅረብ የሚታወቁትን ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያምን ጨምሮ ሌሎች ምሁራንም ታድመዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በዚሁ ጊዜ በሰጡት አስተያየት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአጭር ጊዜ ውስጥ የወሰዷቸው እርምጃዎች አገሪቱን ወደ አንድነት እያሸጋገረ ያለ ለውጥ በመሆኑ እንደሚደግፉትና ለስኬቱም የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል። ከተሳታፊዎቹ መካከል ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም "በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የመጣው ለውጥ በፍቅርና ይቅርታ ላይ የተመሰረተ ነውና ሊጨናገፍ አይገባውም፤" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየሄዱበት ያለው መንገድ "የፍቅር ባቡር ነው"ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ "ሁላችንም በባቡሩ ተሳፍረን መሄድ ይጠብቅብናል" ሲሉም ተናግረዋል። ዶክተር ብርሃነመስቀል ሰኚ የተባሉ ሌላ ኢትዮጵያዊ በበኩላቸው "የኢትዮጵያ ሕዝብ የአስተዳደር ቀመር እጦት እንጂ እርስ በርስ ችግር የለበትም፤ ወደፊትም የአገሪቱን ጉዞ ለማስቀጠል ብዙህነቱን ጠብቆ ከውህደት ይልቅ የአብሮነትና አንድነት ፖሊሲ መከተል ይገባል፤" ብለዋል። "አንድነት ማለት አንድ አይነትነት አይደለም" ያሉት ዶክተር ብርሀነመስቀል፤ እንደ ታሪካዊ አመጣጣቸው በአብሮነት ትስስር ተፈጥሮ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ ብዙህነት ተከብሮ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካ፣ በሳይንስ ተወዳዳሪ ሕዝቦች መሆን ይገባል ሲሉም ገልፀዋል። ለዚህ ዕውን መሆን ደግሞ የዶክተር ዐቢይን የመደመርና የፍቅር እሳቤ መከተል እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት። የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትን ለረጅም ጊዜ የመሩትና የቀድሞው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ዓለም አቀፍ አመራር የነበሩት አቶ ብርሃነ መዋ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የምንፈልገውን ለውጥ ለማምጣት ከዶክተር ዐቢይ ጎን መቆምና ማገዝ ግድ ነው ብለዋል። በአገሪቱ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ሁሌም ያለመደማመጥ ችግር በስፋት እንዳለ የሚጠቅሱት አቶ ብርሃነ፣ በአሁኑ ወቅት ግን የሀሳብ ብዙህነትን ማክበርና መደማመጥ እንደሚገባ ገልጸዋል። ሌሎች የውይይቱ ተሳታፊዎችም የጠቅላይ ሚኒስትሩን አመራር በማድነቅ፤ ወደፊትም ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል። በሌላ በኩል በሰሜን አሜሪካ የኢዜአ ወኪል ዘገባ እንደሚያሳየው ከአሜሪካ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ቤት እንዳይላክ ለማድረግ ይንቀሳቀስ የነበረው ግብረ-ኃይል በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የክልከላ ተግባሩን ማቆሙን ይፋ አድርጓል።