ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ባህልና ትውፊት ለተለያዩ አገራት መሪዎች ማሳየት ኩራትም ክብርም ነው

የካቲት 03 / 2012 ( ኢዜአ ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የባህል ቡድን አባላት  ለአገራት መሪዎችና እንግዶች  በሚያደርጉት አቀባበል ክብርና ኩራት እንደሚሰማቸው ተናገሩ። የባህል ቡድኑ ሰሞኑን ለተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ወደ አዲስ አበባ ለገቡ እንግዶች በኢትዮጵያዊ ባህል አቀባበል አድርጓል። በአዲስ አበባ ሰሞኑን በተካሄደው 33ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ ከተለያዩ አገራት የታደሙ 33 ፕሬዚዳንቶች ፣ 7 ጠቅላይ ሚኒስትሮችና 3 ምክትል ፕሬዚዳንቶች ተገኝተዋል። በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱም ለመሪዎች በሚደረግ ደማቅ ስነ ስርአት አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የፌዴራል ፖሊስ የማርች ባንድ፣ የክብር ዘብና የብሔራዊ ቴአትር የባህል ቡድኖች ለእንግዶቹ አቀባበል ካደረጉት መካከል ናቸው። የብሔራዊ ትያትር የባህል ቡድን አባላት ደግሞ በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አልባሳት አጊጠው የተለያዩ ውዝዋዜዎችንና ዜማዎችን እያዜሙ ሲቀበሉ ሰንብተዋል። ከ19ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ጀምሮ ላለፉት 14 ዓመታት ለመሪዎት የኢትዮጵያን ባህላዊ ውዝዋዜ ሲያሳዩና ሲቀበሉ የቆዩት አንዱ አቶ ኩሲዬ ቶሎንቄ ናቸው። አቶ ኩሲዬ  እንደሚሉት መሪዎች ከዘመናት በፊት ጸረ ቅኝ ግዛት ትግል አድርገው ነጻነታቸውን አውጀው ጉባኤው ለአንድነታቸው የሚመክሩበት በመሆኑ ልዩ ነው። በዚሁ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የሰው ዘር መገኛ ወደ ሆነችው መዲናቸው ኢትዮጵያ ሲመጡ በመቀበላቸው ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸዋል። የሕብረቱ ጉባኤም ከዓመት ዓመት ልዩ ትኩረት እየተሰጠው መምጣቱን ገልጸው ዘንድሮም በልዩ ሁኔታ ለመሪዎቹ ኢትዮጵያዊ አቀባበል ተደርጎላቸዋል ብለዋል። የባህል ቡድኑ አባል የሆነችው ድምጻዊትና ተወዛዋዥ መቅደስ ገብረማሪያም የትያትር ቤቱ አባል ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ የአቀባበሉ ተሳታፊ መሆኗን ትናገራለች። እንግዶችን ሲቀበሉ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ባህላዊ ጨዋታዎች በማሳየት የኢትዮጵያን ብዝሃነት ማሳየት መቻላቸውን ትናገራለች። መሪዎቹም በሚመለከቱት ነገር ደስተኛ ከመሆናቸው አልፎ አንዳንዶቹ ከቡድኑ ጋር ወዝ ወዝ እንደሚሉም የሚናገረው ደግሞ ሌላው የትያትር ቤቱ አባል በረከት ባዩ ነው። ይህንን እድል አግኝቶ በመሪዎች ፊት አገርን ወክሎ መከወን በራሱ የተለየ ስሜትና ደስታን ያለብሳልም ነው ያለው። አንጋፋው የብሔራዊ ቴአትር በተለያዩ አገራዊ ክንውኖች ላይ በስፋት እየተሳተፈ የኢትዮጵያን ባህላዊ ትውፊቶችና መልካም ገጽታዎች ለዓለም የማስተዋወቅ ስራ ይሰራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም