በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ምልክት ታይቶበት በለይቶ ማቆያ ማዕከል የሚገኝ ሰው አለመኖሩ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ምልክት ታይቶበት በለይቶ ማቆያ ማዕከል የሚገኝ ሰው አለመኖሩ ተገለጸ
አዲስ አበባ ( ኢዜአ) የካቲት 3/2012 በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የኖቬል ኮሮና ቫይረስ ምልክት ታይቶበት በለይቶ ማቆያ ማዕከል የሚገኝ ሰው አለመኖሩን የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኖቬል ኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ እንደገለጹት፤ የቫይረሱን ስርጭት አስመልክቶ እስካሁን 39 ጥቆማዎች ደርሰው በጥቆማዎቹ መሰረት የማጣራት ሥራ ተከናውኗል። በዚህም 14 ሰዎች የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው ስለነበረ ተለይተው ወደ ማቆያ ስፍራ እንዲገቡ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩን አስታውሰዋል። ይሁንና "በተደረገው የላቦራቶሪ ምርመራም ሰዎቹ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል" ብለዋል። በትናትናው ዕለት አንድ ሰው በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረ ሲሆን በኢንስቲትዩቱ የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ ውጤቱ ከቫይረሱ ነፃ በመሆኑ ከማዕከሉ መውጣቱን ዶክተር ኤባ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የበሽታው ምልክት ታይቶበት ወደ ለይቶ ማቆያ ማዕከሉ የገባ ምንም ሰው አለመኖሩን አስታውቀዋል። ሕብረተሰቡ እስካሁን በአገሪቱ በኮሮና ቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠ ሰው አለመኖሩን አውቆ ሳይዘናጋ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል። የኮሮና ቫይረስ ከታየባቸው አገራት የመጡ መንገደኞች ወይም በቫይረሱ ከተያዙ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ላይ እንደ ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥ እንዲሁም የመተንፈስ ችግርና መሰል የበሽታው ምልክቶች ከታዩ ሕብረተሰቡ በ"8335" ነጻ የስልክ መስመር ደውሎ እንዲጠቁምም ጥሪ አቅርበዋል። ስለበሽታው ግንዛቤ ለመፍጠር ለመገናኛ ብዙሀንና ለሆቴል ባለሙያዎች እንዲሁም ከክልልና ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለተውጣጡ ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን አባላት ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል። ዶክተር ኤባ እንዳሉት ከቻይና የሚመጡ መንገደኞችን የሙቀት ልየታና የበሽታው ምልክት የታየባቸውን መንገደኞች የጤና ሁኔታ የመከታተል ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል። የኢንዱስትሪ ፓርክ ባለባቸው ሁሉም ክልሎች ውስጥ የለይቶ ማቆያ ማዕከልና የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ማስተባበሪያ ማዕከላት በማቋቋም ለምላሽ ዝግጁ ለማድረግም ዕቅድ ተይዟል። ለዚህም በደቡብ ክልል ሃዋሳ ከተማ ድጋፍ ሰጪ የባለሙያዎች ቡድን በመላክ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን የዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። የኮሮና ቫይረስ ዝግጁነትና ምላሽ እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሁሉም አቅጣጫዎች በሚገኙ የአገሪቷ መውጫና መግቢያ ድንበሮች የሙቀት ልየታ ሥራ እየተከናወነ ነው። ለዚህም ከጥር 14 እስከ የካቲት 2 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የኮሮና እና የኢቮላ ቫይረስን ዝግጁነት በጋራ በማጣመር ከ172 ሺህ በላይ መንገደኞች ላይ የሙቀት ልየታ መደረጉን የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያሳያል። የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 43 ሺህ 108 የደረሰ ሲሆን ቫይረሱም በ25 አገራት ተከስቷል። በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 1 ሺህ 18 ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን 4 ሺህ 53 የሚሆኑት ደግሞ ከበሽታው ማገገም ችለዋል ተብሏል።