"ቨርሚ" የተባለው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ሆኖልናል ---አርሶአደሮች - ኢዜአ አማርኛ
"ቨርሚ" የተባለው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ሆኖልናል ---አርሶአደሮች
ደብረብርሃን የካቲት 3ቀን 2012 "ቨርሚ" የተባለውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ የገቢ ምንጭ እንደሆነላቸው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ገለጹ። "ቨርሚ" ገለባ፣ የእንስሳት ፍግ፣ አፈር፣ ቅጠላ ቅጠሎችንና ተረፈ ምርቶችን በትሎች አማካኝነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲበሰብስ በማድረግ ለግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብአት የሚያገለግል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ኮምፖስት የማዘጋጀት ሒደት ነው ።
አርሶ አደሮቹ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው ምርትና ምርታማነታቸውን ከማሳደግ በተጨማሪ በማባዛት አንዱን ኪሎ ግራም በ500 ብር ሒሳብ በመሸጥ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ይናገራሉ ።
የሞጃና ወደራ ወረዳ ፈረስ መጋለቢያ ቀበሌ አርሶ አደር አስፋው ወልደፃዲቅ ለኢዜአ እንደገለጹት የቨርሚ ኮምፖስትን ማዘገጃት የጀመሩት ባለፈው ዓመት "ይፋድ’’ በተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት አማካኝነት በተደረገላቸው ድጋፍ ነው ።
ድርጅቱ ትሎችን ከምስራቅ ጎጃም ዞን አስመጥቶ እንደሰጣቸው የሚናገሩት አርሶ አደሩ ተገቢውን ስልጠና ከወሰዱ በኋላ የቨርሚ ኮምፖስት በአግባቡ በማዘጋጀትና በማሳቸው ላይ በመጨመር የመስኖና የመኸር ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደቻሉ ተናግረዋል ።
ቨርኒ ኮምፖስት ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱ መስራች ትሎችን አባዝተው አንዱን ኪሎ ግራም ለአካባቢው አርሶ አደሮች በ500 ብር ሒሳብ በመሸጥ 27 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ ማግኘታቸውነ ገልፀዋል ።
ሌላው የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ገረመው ለማ በበኩላቸው የቨርሚ ኮምፖስትን ባለፈው ዓመት አዘጋጅተው በማሳቸው በመጠቀማቸው ምርታማነታቸው በእጥፍ ማሳደግ ችለዋል።
በተጨማሪም የሚያባዙትን መስራች ትል ለአካባቢ አርሶ አደሮች በመሸጥ ባለፉት ወራት ብቻ 13 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ በማግኘታቸው በቀጣይ በስፋት ለመስራት መነሳሳታቸውን ተናግረዋል።
በደብረብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል የአፈር ለምነት ተመራማሪ አቶ ቀንዘመድ ካሴ እንደገለጹት ቨርሚ ኮምፖስት ገለባ፣ የእንስሳት ፉግ፣ አፈር፣ ቅጠላ ቅጠሎችንና የተረፈ ምርቶችን በትሎቹ እንዲበሰብስ በማድረግ የሚዘጋጅ ተመራጭ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ነው።
የቨርኒ ኮምፖስት ለሰብል እድገት አስፈላጊ የሆኑ እንደ ፎርፎረስ፣ ናይትሮጅን፣ ፖታሽየምና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን የያዘ በመሆኑ ለአርሶአደሩ ምርታማነት ተመራጭ መሆኑን አስረድተዋል ።
በተለይም ወጣቶችንና ሴቶችን በቨርኒ ኮምፖስት መስራች የትል ዝርያ በቀላሉ እያባዙ ለአርሶ አደሮች በመሸጥ አዋጪና ተመራጭ የስራ ዘርፍ የሚፈጥርላቸው በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል ።
የምርምር ማዕከሉ በአርሶ አደሮች የተጀመረውን የቨርኒ ኮምፖስት ዝግጅት በዘላቂነት ለማሳደግ በኤፍራታና ግድም ወረዳ ስነምህዳሩን መሰረት ያደረገ ምርምር በማካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የአፈር ለምነት ባለሙያ ወይዘሮ እመቤት ዘለቀ እንዳሉት በሞጃና ወደራ ወረዳ 150 አርሶ አደሮች የቨርኒ ኮምፖስትን እያዘጋጁ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂውን ወደ ሌሎች የዞኑ ወረዳዎች ለማስፋትም በስድስት ወረዳዎች በሚገኙ የገበሬ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ትሉን በማሰራጨት የማባዛትና የመመራመር ተግባር እየተካነወነ መሆኑን አስረድተዋል ።
በዞኑ ዚህ አመት ከ164 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ የቨርኒ ኮምፖስትን ጨምሮ ሶስት ነጥብ ሶስት ሚሊየን ሜትር ኩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ ።