በአፋር ክልል ለመስኖ የተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶች አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸው የነዋሪዎች ቅሬታ አስነሳ

64
አፋር፣ የካቲት 3/2012 (ኢዜአ) በአፋር ክልል አላይደጌ የግጦሽ መሬት አካባቢ የተቆፈሩ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች አገልግሎት ሳይሰጡ ለዓመታት መቆየታቸው በነዋሪዎች ቅሬታ አስነስቷል። የክልሉ መንግስት በበኩሉ የውሃ ጉድጓዶቹ በበጀት እጥረት ምክንያት የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ሳይገጠምላቸው ለዓመታት መቆየታቸውን ገልጾ፤ በአሁኑ ወቅት የፓምፕ ግዥ እየተከናወነ መሆኑንና በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡ አስታውቋል። እንደ አውሮጳዊያኑ የዘመን ቀመር ከ2006 ጀምሮ ከ206 ሺህ ሄክታር በላይ ስፋት ባለው አላይደጌ የግጦሽ መሬት ላይ የተለያዩ ሰብሎችን በመስኖ ለማልማትና ለእንስሳት መኖ ለማዘጋጀት 53 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል። ይሁን እንጂ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶቹ የውሃ መሳቢያ ሳይገጠምላቸውና ምንም አገልግሎት ሳይሰጡ ለዓመታት በመቀመጣቸው ነዋሪዎችን ቅር አሰኝቷል። በአፋር ክልል አሚባራ ወረዳ የአላይደጌ ቀበሌ አርብቶ አደር አቶ አቡበከር መሀመድ እንዳሉት የፌዴራል መንግስት ለእንስሳት መኖ ልማትና ለመስኖ ሥራ የሚውሉ የውሃ ጉድጓዶችን ማስቆፈሩን ሰምተዋል። ይሁን አንጂ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶቹ ከተቆፈሩ በኋላ ምንም አይነት አገልግሎት ሳይሰጡ ተደፍነው ዓመታትን አስቆጥረዋል ይላሉ። ከአካባቢው አልፎ ለአገር የሚሆን፣ ለከብት እርባታና ለግብርና ሥራ የሚያገለግል በቂ መሬት መኖሩን የገለጹት አቶ አቡበከር መንግስት ጉድጓዶቹን ወደ አገልግሎት እንዲያስገባ ጠይቀዋል። የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተርና ተመራማሪ አቶ ብርሃኑ መገርሳ በበኩላቸው የአላይደጌ የግጦሸ መሬት በኢትዮጵያ ቆላማ ቦታዎች ወደ እርሻ ሊቀየሩ ከሚችሉ መሬቶች ግንባር ቀደሙ መሆኑን ነው የገለጹት። አካባቢው እምቅ የከርሰ ምድር ውሃ ክምችት ያለው ከመሆኑም ባለፈ ለመጠጥ ውሃ፣ ለእንስሳት መኖ ዝግጅትና የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችን በመስኖ ለማልማት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል። "ለሜካናይዝድ እርሻ ምቹ መሬት መሆኑንም በጥናት አረጋገጠናል" ብለዋል። ፓምፕ ሳይገጠምላቸው የታሸጉት የውሃ ጉድጓዶች አገልግሎት መስጠት ከቻሉ አዋጭ የግብርና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ወደሥራ ማስገባት እንደሚቻል ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የቆላማ አካባቢዎችን በመስኖ በማልማት የግብርና ምርትን ለማሳደግ እንደ አላይደጌ እምቅ አቅም ላላቸው አካባቢዎች ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባም ነው አቶ ብርሃኑ ያመለከቱት። በተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክቶች አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ታደሰ ከተቆፈሩት 53 የውሃ ጉድጓዶች 14ቱ ለጥናት የተቆፈሩ መሆናቸውን ይናገራሉ። "ከፍተኛ የውሃ ክምችት መኖሩን ካረጋገጥን በኋላ እስከ 550 ሜትር ጥልቀት ያላቸው 39 አገልግሎት የሚሰጡ ጉድጓዶች ቆፍረናል" ብለዋል። ከእነዚህ መካከል 15ቱ ሥራ መጀመራቸውን ገልጸው ቀሪዎቹን ለአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ማስረከባቸውንና ወደ ሥራ ለማስገባትም በጀት እየተፈለገ መሆኑን ተናግረዋል። የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው፣ የተቆፈሩ ጉድጓዶች በበጀት ምክንያት አገልግሎት ሳይሰጡ በመቆየታቸው በህብረተሰቡ ላይ ቅሬታ መፈጠሩን አስታውሰዋል። በበጀት ችግር ምክንያት ቶሎ ወደስራ ባለመግባታቸው ችግሩ እስከ ቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ድረስ ቀርቦ እንዲታወቅ መደረጉንም አመልክተዋል። "በአሁኑ ወቅት ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ለመጠቀም የውሃ ፓምፖች ግዥ ታዝዞ በሂደት ላይ በመሆኑ ጉድጓዶቹ በቅርቡ ሥራ ይጀምራሉ" ብለዋል። በአላይደጌ ካለው ሰፊ የግጦሽ መሬት በተጨማሪ እያንዳንዳቸው እስከ 100 ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት የሚችሉ ከመቶ በላይ የውሃ ጉድጓዶችን መቆፈር የሚያስችል እምቅ የውሃ ክምችት መኖሩን ጥናቶች ያሳያሉ።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም