ጉባዔው የአህጉሪቷን ሁለንተናዊ ዕድገትና አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች ተላልፈውበታል - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
ጉባዔው የአህጉሪቷን ሁለንተናዊ ዕድገትና አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች ተላልፈውበታል - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
አዲስ አበባ ፣የካቲት 3/2021 (ኢዜአ) የአፍሪካ ኅብረት 33ኛ የመሪዎች ጉባዔ መጠናቀቁን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉባዔው የአፍሪካ ኅብረትን ወደ ተሻለ ደረጃ ያደረሰ ሲሆን፤ የአህጉሪቷን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ዕድገትና አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች ተወስነውበታል ብለዋል።
በዚህ ጉባዔ 32 የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች፣ ሶስት ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ሰባት ጠቅላይ ሚኒስትሮችና ሶስት ከአፍሪካ ውጭ የመጡ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተሳትፈውበታል።
"የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ለድርጅቱ ጥንካሬ የአልማዝ መሰረት ሆና ኖራለች። ለአፍሪካዊያን ነጻነት ያደረገችው ትግል ሲሳካ የአፍሪካዊያን ሁለንተናዊ አንድነት እንዲመጣ ጥረት አድርጋለች፤ በማድረግም ላይ ትገኛለች" ብለዋል።
"ይህ ትግልና ጥረት የኢትዮጵያ መንግስታት በዘመናት ያልቀያየሩት አቋማቸው ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብም አብሮት የኖረና የሚኖር እምነት ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "33ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔን ያስተናገድነውም በዚህ መንፈስ ነው" ሲሉ አክለዋል።
የመሪዎቹ ጉባኤ "በተሳካና ሀገራችንን በሚያስመሰገን መልኩ ተጠናቋል" ለዚህ ጉባኤ ስኬት የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ያጋጠመውን የአንዳንድ እንቅስቃሴዎች መስተጓጎል በጸጋ በመቀበል ከተለያዩ አካላት ለሚሰጡ መመሪያዎች አክባሪ በመሆን የዜግነት ግዴታውን ተወጥቷልም ነው ያሉት።
የፖሊስ አካላት ብርቱና ዘመናዊ የቅድሚያ ልምምድ በማድረግ በአስተማማኝ መልኩ የከተማዋን ጸጥታ ጠብቀዋል፤
የደህንነት አካላት እጅግ ስልጡን በሆነ መንገድ የተቀላጠፈ የመረጃና የደህንነት አገልግሎት ሰጥተዋል። የሪፓብሊካን ዘብ አካላት ለሃያ አራት ሰዓታት የእንግዶቹን አካባቢዎች፣ የጉባኤውን አካባቢና የመመላለሻ መንገዶችን ደህንነት በማስጠበቅ የብረት በር ሆነዋል።
ባለሆቴሎችና የሆቴል አገልጋዮች ኢትዮጵያን የሚያስመሰግን መስተንግዶ አቅርበዋል፤ ዲፕሎማቶችና የፕሮቶኮል ባለሙያዎች ሂደቶች በሙሉ ደረጃቸውን የጠበቁና የተቀላጠፉ እንዲሆኑ አስችለዋል ይላል የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት።
የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የሠመረ አገልግሎት አበርክተዋል፤ ሌሎች ወገኖችም የሚጠበቅባቸውን በመወጣት ኢትዮጵያ የብርቱዎች አገር መሆንዋን አስመስክረዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ፤ "ሁሉም አካላት ላደረጉት አገር የሚያኮራ ተግባር በራሴና በኢትዮጵያ መንግስት ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ" ብለዋል።
ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ አቅሞቻችንን ሁሉ አስተባብረን ሕመሞቻችንን ሁሉ ተቋቁመን ከሠራን እንዴት ውጤታማ እንደምንሆን የዚህ ጉባኤ ስኬት ብዙ ነገሮችን ያስተምረናል። አፍሪካዊያን እህቶቻችንና ወንድሞቻችን በመስተንግዷችንና በተቀላጠፈው አገልግሎታችን ተደስተዋል።
ይህም "አዲስ አበባ ዋና ከተማቸው መሆኗን በተግባር እንዲያረጋግጡ አድርጓቸዋል"።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን መልካም ስም ለብዙ አፍሪካዊ ስኬቶች መጠቀም አለብን ሲሉም በመልዕክታቸው አስገንዝበዋል።
"አፍሪካዊያን በጋራ ለመስራት፣ ለመማማር፣ በጋራ ለመነገድ፣ በጋራ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠርና በጋራ ሀብቶቻችንን ለማልማት ዕድል እንዳለን አይተናል" በማለት ገልጸዋል።
"በመደመር ዕሳቤ ጠንካራ ውስጣዊ አቅምና አንድነትን ፈጥረን የተሻለች አፍሪካን ወደ ማየት መሸጋገር አለብን" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "መጀመሪያ እኛ እርስ በእርሳችን ተናበንና ተገናዝበን በመስራት ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አቅም እንፍጠር፤ ቀጥሎም ከጎረቤቶቻችን ጋር ቀጠናዊ ትስስር፣ ትብብርና ትግግዝን እናስፋፋ" ነው ያሉት።
ከዚያም አፍሪካዊያን በዓለም ላይ አንድ ሆነን በጋራ የምንቆምበት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሃይል እንገነባለን። ለዚህም በትንሽ በትልቁ ጉልበታችንን፣ ጊዜያችንን መጨረሱን ትተን ማርሽ በሚቀይር ነገር ላይ አቅማችንን እንድናውለው ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ "በድጋሚ ይህ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እንዲሳካ ሌት ተቀን ለሠራችሁ ሁሉ ምስጋናዬን እያቀረብኩ የአገራችን የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ ይህ ትጋት እንዲቀጥል አደራ እላለሁ" ሲሉ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።