በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተመራ ልዑክ ናይሮቢ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተመራ ልዑክ ናይሮቢ ገባ
አዲስ አበባ ፣የካቲት 3/2012 (ኢዜአ) በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተመራ የልዑካን ቡድን በቀድሞ የኬንያ ፕሬዚደንት ዳንኤል ቶሮይቲች አራፕ ሞይ ብሔራዊ የቀብር ስነ-ስርዓት ላይ ለመገኘት ናይሮቢ ገባ። የልዑካን ቡድኑ ዛሬ ጠዋት ጆሞ ኬኒያታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የኬንያ ቱሪዝምና ዱር ኃብት ሚኒስትር ነጂብ ባላላና ሌሎች የአገሪቷ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም በኬንያ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለምና የኤምባሲው ዲፕሎማቶች አቀባበል አድርገውለታል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጥር 27 ቀን 2012 ዓ.ም ለኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ በላኩት የሀዘን መግለጫ በቀድሞው ፕሬዚደንት ህልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በኢትዮጵያ ሕዝብና በራሳቸው ስም ገልፀዋል። አራፕ ሞይ ለኬንያ ነፃነት ያደረጉትን ተጋድሎ ያስታወሱት ፕሬዚዳንቷ በቀጠናዊው በይነ-መንግስታት ኢጋድ ምስረታ እንዲሁም በአህጉራዊ ሠላምና ልማት ጉልህ ሚና እንደተጫወቱም ጠቅሰዋል። ሁለተኛው የኬኒያ ፕሬዚዳንት ቢያልፉም ለሕዝባቸውና ለአፍሪካ ደህንነት ባደረጉት በጎ ተግባር ሁሌም እንደሚታወሱ ጠቅሰው ለኬኒያዊያን፣ ለኬንያ መንግስትና ለሟቹ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ቤተሰቦችና ወዳጆች መፅናናትን ተመኝተዋል። ዳንኤል ቶሮይቲች አራፕ ሞይ ከጥቅምት 04 ቀን 1971 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 21 ቀን 1995 ዓ.ም ድረስ ኬንያን በርዕሰ ብሔርነት መርተዋል።