ጉባዔው በሊቢያና በሳህል ቀጣና ያለውን ቀውስ ለመፍታት አጀንዳ አድርጎ በዝግ ስብሰባ ሲመክር ቆየ - ኢዜአ አማርኛ
ጉባዔው በሊቢያና በሳህል ቀጣና ያለውን ቀውስ ለመፍታት አጀንዳ አድርጎ በዝግ ስብሰባ ሲመክር ቆየ
የካቲት 2/2012 (ኢዜአ) የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባዔ ለሁለት ቀናት በዝግ ባካሄደው ውይይት በሊቢያና በሳህል ቀጣና ያለው ቀውስ ለመፍታት አጀንዳ አድርጎ ሲመክር መቆየቱን የኀብረቱ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ኮሚሽነር አምባሳደር ስማይል ቼርጉይ ገለጹ። ''ለአፍሪካ ልማት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የጦር መሳሪያ ድምጽን ማጥፋት'' በሚል መሪ ሃሳብ በመካሄድ ላይ ያለው የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባዔ ዛሬ ማምሻውን ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት በአህጉሩ ባለው የሊቢያና የሳህል ቀጣና ቀውስ ዙሪያ መፍትሄ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። እንደ ኮሚሽነር ቼርጉይ ማብራሪያ፤ ከቀናት በፊት በርዋንዳና በኡጋንዳ መካከል ያለውን የድንበር ጉዳይ ለመፍታት ውይይት ተካሂዶ ነበር። በሊቢያ ያለውን ቀውስ ለመፍታት ከሰላምና ፀጥታ ምክር ቤቱ በተጨማሪ የከፍተኛ ደረጃ ኮሚቴ ሊቀመንበር በሆኑት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝና የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በተመራ የልዑካን ቡድን መካከል ውይይት መካሄዱን አብራርተዋል። እንዲሁም በሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊናና በአካባቢው ያለውን ጉዳይ የሚያጠናና ሰላም ለማስፈን የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን የሚያመቻች የታዛቢ ቡድን ወደ ስፍራው ለመላክ ተመድ ጣልቃ እንዲገባ ይፋዊ ስምምነት መደረጉን ጠቁመዋል። በሊቢያ ሰላም ለማምጣት ከሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ውጭ የኀብረቱ አባል አገሮች ጣልቃ እንዳይገቡ በተመድ የተቀመጠው ገደብ እንዲከበር መሪዎቹ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል። ከሊቢያ እስከ ሳህል ቀጣና ድረስ በታጣቂ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋለ አካባቢ መሆኑንም ጠቁመዋል። በአካባቢው ያለው አሸባሪ ኃይል አዲስ ቴክኒክ በመጠቀም በንጹሃን ዜጎች ላይ ከሚያደርሰው ግድያ በተጨማሪ በፀጥታ ኃይሎችና ተቋማት ላይም ጥቃት እየፈጸመ እንደሚገኝም አመልክተዋል። በሳህል ባሉ አምስት አገሮችና በቀጣናው ያለው ቀውስ በኀብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ችላ የሚባል ጉዳይ ሳይሆን በሰፊ ውይይት የተደረገበት እንደሆነም ገልጸዋል። ‘’አሸባሪዎችን የመዋጋት ጉዳይ ዓለማቀፋዊ ነው’’ ያሉት ኮሚሽነሩ በአህጉሩ ባሉ አገሮች ዘንድ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ እንደሆነም አብራርተዋል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በሳህል እና በቀጣናው ያለው ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አምባሳደር ቼርጉይ ጥሪ አቅርበዋል። በሁለቱ ተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በአገሪቱ የሽግግር መንግስት ለመመስረት የተሰጠው የ100 ቀን የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ 12 ቀናት እንደቀሩትም አብራርተዋል። የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት በቀሩት ቀናት የሽግግር መንግስቱን የማይመሰርቱ ከሆነ የአፍሪካ ኀብረት ተጨማሪ ቀን እንደማያራዝምም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። በሱዳን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ በጥሩ መንገድ እየሄደ ሲሆን የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየደቀቀ መሄድ ኀብረቱን የሚያሳስበው እንደሆነም ተናግረዋል።