ካናዳውያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች መሳተፍ ይፈልጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ካናዳውያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች መሳተፍ ይፈልጋሉ
የካቲት 2/2012 (ኢዜአ) የካናዳ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸውን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ። በአዲስ አበባ ለሶስት ቀናት የተካሄደው የኢትዮጵያና ካናዳ የቢዝነስ ፎረም ዛሬ ተጠናቋል። ፎረሙ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰት ይበልጥ ለማሳደግ አስተዋጽኦ እንዳለው ተጠቁሟል። የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ ከካናዳ የንግድ ሚኒስትር ሜሪ ኤንጂ ጋር ካናዳውያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ማውጣት ስለሚችሉበት ሁኔታ ተወያይተዋል። ኮሚሽነሩ በውይይቱ የኢትዮጵያ መንግስት እያካሄደው ስላለው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርምና ካናዳውያኑ ባለሀብቶች ኢንቨስት ቢያደርጉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ለንግድ ሚኒስትሯ መግለፃቸውን ተናግረዋል። ካናዳ በኢትዮጵያ ያላት ኢንቨስትመንት አነስተኛ በመሆኑ ተሳትፎዋን ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል። በሁለቱ አገራት መካከል የኢንቨስትመንት ጥበቃና ማስፋፊያ የሁለትዮሽ ስምምነት ያልነበረ በመሆኑ ስምምነት ተፈርሞ ተግባራዊ እንዲሆን የንግድ ሚኒስትሯ ሜሪ ኤንጂ ጥያቄ ማቅረባቸውንም ገልፀዋል። ኮሚሽነሩም በቀጣይ በሚካሄዱ ውይይቶችና ድርድሮች የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ጥበቃና ማስፋፊያ ስምምነቶች እንደሚፈረሙ ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል። የካናዳ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በቱሪዝምና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች መዋዕለ ንዋይ ቢያፈሱ አገራቱን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል አብራርተዋል። ኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ እየፈጠረች መሆኑን የጠቀሱት አቶ አበበ ካናዳዊያኑ በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች የመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸውን ተናግረዋል። የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬሕይወት ወልደሃና በበኩላቸው፤ የአገሪቷን የኃይል ምንጮች በተመለከተ ለካናዳ ባለሀብቶች ገለፃ ማድረጋቸውና ባለሃብቶቹም መደሰታቸውን አክለዋል። በመሆኑም ካናዳዊያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በየትኛውም ዘርፍ መሰማራት ቢፈልጉ የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳይኖር መንግስት በትኩረት ይሰራል ብለዋል። የኢትዮ-ካናዳ ማኅበረሰብ የንግድ ምክር ቤት ዳይሬክተርና የመንግስት ህዝብ ግንኙነት የሆኑት ዶክተር ሉምባ ወልደገብርኤልም ኢትዮጵያ ትልቅ የኢንቨስትመንት አቅም ያላት በመሆኗ የካናዳ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎት አላቸው ነው ያሉት። በካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ቱሩዶ የተመራውና ሶስት የካቤኔ አባላትና ባለሀብቶችን ያካተተው ልዑክ የኢትዮጵያ ጉብኝትም የአገሪቷን የኢንቨስትመንት አቅም ማሳያ መሆኑን አክለዋል። የካናዳ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸውና ለተግባራዊነቱም በቀጣይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ገልፀዋል። ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄዳ በቆየው የኢትዮጵያና ካናዳ የቢዝነስ ፎረም ከ20 በላይ የካናዳ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ተሳትፈዋል። በቢዝነስ ፎረሙ የተሳተፉት ከ100 በላይ የኢትዮጵያ ባለሃብቶችም የልምድ ልውውጥ አድርገዋል። የሁለቱ አገራት የንግድ ልውውጥ መጠን በአውሮፓውያኑ የ2018 ዓመት 170 ሚሊዮን ዶላር ነበር። ከዚህ ውስጥ 130 ሚሊዮን ዶላር ካናዳ ወደ ኢትዮጵያ ከላከቻቸው ምርቶች ያገኘችው ነው።