ቀጥታ፡

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ "በቂ እውቀት" ሊኖራቸው እንደሚገባ ተጠቆመ

የካቲት 2/2012 (ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ግንዛቤያቸውን በማስፋት አስተማሪና ትክክለኛ መረጃ ለህብረተሰቡ ሊያደርሱ ይገባል ተባለ። የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ስለ ኮሮና ቫይረስና አገሪቱ እያደረገች ያለውን ቅድመ ጥንቃቄ በማስመልከት ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ለተወጣጡ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል። በኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ ማስተባበሪያ ማዕከል የ2019 ኖቭል ኮሮና ቫይረስ ቅድመ ዝግጁነት ማኔጀር አቶ ዘውዱ አሰፋ እንደተናገሩት ቫይረሱን ለመከላከል በአገር ደረጃ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት ማብራሪያ ሰጥተዋል። የመከላከል ሂደቱንና አጠቃላይ የቫይሰሩን ነባራዊ ሁኔታ በማስመልከት ለማህበረሰቡ መረጃ ለማድረስ እንዲቻል የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በቂ መረጃ እና ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል። የቫይረሱን አጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት ኢንስቲትዩቱ በሚያወጣውን ትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ለህብረተሰቡ ትክክለኛና ተአማኒ መረጃ በማድርስ መገናኛ ብዙሃኑ በትኩረት ሊሰሩ ይገባልም ነው ያሉት። በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በሚተላለፉ ትክክለኛ ባልሆኑ መረጃዎች ሰዎች "ግራ መጋባት ውስጥ እየገቡ" መሆኑንም አስታውሰዋል። የተረጋገጡ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ ኢንስቲተዩቱንና የሚመለከታቸውን አካላት በመረጃ ምንጭነት መጠቀም ይገባል። በአገሪቱ ቫይረሱ እንዳይከሰት እየተደረገ ያለውን ጥንቃቄ በሚመለከትም የኢትዮጰያ አየር መንገድን ጨምሮ በመግቢያና መውጫ በሮች ተገቢ ቁጥጥሮች እየተደረጉ ይገኛሉ። በሚደረገው ቁጥጥርና ጥቆማ መሰረትም ናሙናዎችን በማሰባሰብ እየተመረመሩና ውጤታቸው እየተረጋገጠ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ ከተጠረጠሩና ክትትል እየተደረገባቸው ካሉ ዜጎች ውጭ ምንም አይነት የተለየ የቫይረሱ ምልክት አለመታየቱን አረጋግጠዋል። የኤርፖርት ታክሲ ሾፌሮች፣ የኢንተርናሽናል ሆቴሎች ሙያተኞች፣ ጋዜጠኞችና የጤና ባለሙያዎች ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። የቫይረሱ መመርመሪያ መሳሪያ አገር ውስጥ ገብቶ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ምርመራ እየተከናወነ ሲሆን የምርመራ ውጤቱም በደቡብ አፍሪካ ከተደረገው ምርመራ ጋር ተመሳክሮ የመሳርያው ጥራትና ትክክለኛነት ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት። በአዲስ አበባ በተለዩ አካባቢዎች ላይ አምስት የማቆያ ማእከላት ተዘጋጅተው ተጠርጣሪዎች በማእከላቱ ቆይተው ክትትል የሚያደርጉበት ሁኔታ መኖሩንም እንዲሁ። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ግብረ ሓይል፣ በጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ በኢትዮጰያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተና በኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ ማስተባበሪያ ማዕከል የሚመራ አራት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የቅድመ መከላከል ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል። ግብረ ሃይሉ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ በትኩረት እየሰራ ሲሆን በሳምንት ሰባቱንም ቀናት ለ24 ሰዓት በመስራት ላይ መሆኑን አቶ ዘውዱ ተናግረዋል። ቫይረሱን በተመለከተ 29 ሰዎች ተጠርጥረው ለኢንስቲትዩቱ ጥቆማ ደርሶ ከነዚህ ውስጥ 14ቱ በተለየ ማቆያ ሆነው ምርመራ ተደርጎላቸው ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል። በቻይና በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ እስካሁን 40 ሺህ 171 ቻይዊያን በቫይረሱ ሲያዙ ከ25 ባላነሱ የአለም አገራትም የቫይረሱ ምልክት ታይቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም