ቀጥታ፡

ከ13 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ፍቅርና አንድነቱን በሚደምሩ ተግባራት ላይ ይሳተፋሉ

አዲስ አበባ ሰኔ 20/2010 በዘንድሮው ክረምት በጎ ፈቃድኛ ወጣቶች ፍቅርና አንድነቱን በሚደምሩ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ መታቀዱን የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌደሬሽን አስታወቀ። በዘንድሮው ክረምት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ13 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃድኛ ወጣቶችን ወደ ስራ ማስገባት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንም ገልጿል። በዚሁ መሠረት ፌደሬሽኑ እስካሁን ወጣቶች በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤያቸው እንዲጎልበት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ኮሚቴና ፈጻሚ አካላትን ማዋቀርና እቅድ የማዘጋጀት ስራ መሠራቱን ገልጸዋል። በተጨማሪም ፌደሬሽኑ ሰኔ 18 ቀን 2010ዓ.ም በአዳማ ከተማ አገልግሎቱን በይፋ ለመጀመር የሚያስችለውን የመክፈቻ ስነ ስርዓት አካሄዷል። የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ወጣት ታረቀኝ አብዱልጀባር ለኢዜአ እንደገለጸው የክረምት ትምህርት፣ ደም ልገሳ፣ የተፋሰስ ልማትና ችግኝ ተከላና የመንገድ ትራፊክ ደህንነት በበጎፈቃደኞች ከሚሰሩት ስራዎች ውስጥ ናቸው። የጎዳና ወጣቶች የስራ እድል የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸትና ወደ መጡበት አካባቢ የመመለስ፣ አረጋውያንን መርዳት፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ ግንዛቤ መስጠት በወጣቶቹ የሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ናቸው ብሏል። በዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአዲስ መልክ እንዲካተት የተደረገው ጉዳይም ወጣቱ በአገራዊ አንድነት ዙሪያ ግንዛቤው እንዲዳብር የሚያስችል ስልጠና እና ውይይት እንደሚካሄድም ፕሬዝዳንቱ አክሏል። ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ ከ13 ሚሊዮን  በላይ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በተለያዩ መስኮች በመሰማራት አገልግሎት ለመስጠት የዝግጅት ምዕራፋቸውን እንዳጠናቀቁ ነው የገለጸው። በተጨማሪም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ወደ ተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በማቅናት አገልግሎት እንደሚሰጡ የገለጸው ፕሬዝዳንቱ፣ አገልግሎቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱንም ለማጠናከር እድል ይፈጥራል ብሏል። በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊውን እገዛና እርዳታ የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ተገልጿል፡፡ አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስችል ግብዓት ለማሟላት አገልግሎቱ ከሚሰጥባቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውንም ገልጿል። ባለፈው ዓመት በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በገንዘብ ሲተመን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ ሥራዎች ያለክፍያ መከናወናቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም