ቀጥታ፡

ለመጪው የምርጫ ስኬት የበኩሉን እገዛ ለማድረግ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር አስታወቀ

አዲስ አበባ የካቲት 02/2012 ( ኢዜአ) ለመጪው ብሄራዊ ምርጫ ስኬታማነት የበኩሉን እገዛ ለማድረግ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር አስታወቀ። በኢትዮጵያ   ለስድስተኛ  ጊዜ ለሚካሄደው ብሄራዊ ምርጫ በምርጫ ቦርድ በኩል አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል በቅርቡ የምርጫ ሂደቱ መርሃ ግብር ይፋ መደረጉም ይታወቃል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ለምርጫው ስኬታማ ክንውን የበኩሉን እገዛ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋል። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኢድሪስ መሃመድ እንደሚሉት ማህበሩ እንደ አንድ የሲቪክ ማህበር ምርጫው ሰላማዊና የተሳካ እንዲሆን እገዛ ለማድረግ ተዘጋጅቷል። ማህበሩ በምርጫ ቦርድ በኩል የሚጠየቀው ማንኛውም ድጋፍና እገዛ ካለ የሚችለውን ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል። እንደ አቶ ኢድሪስ ገለፃ በተለያዩ የውጭ አገራት የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በብዙ መልኩ እገዛ ለማድርግ ዝግጁ ናቸው። የዳያስፖራው ማህበረሰብ ባለው እውቀት፣ ክህሎትና የገንዘብ አቅም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት አለውም ነው ያሉት። በዚህም የምርጫ ቦርዱ የሚጠይቀው እገዛ ካለ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር አገራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት የተቻለውን ሁሉ ድጋፍና እገዛ ያደርጋል ብለዋል። በአገር ውስጥ እየተፈጠሩ ላሉ የሰላም መደፍረስ ምክንያት እየሆኑ ያሉ በውጭም ይሁን በአገር ቤት የሚኖሩ ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸውን አሳስበዋል። በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት፣ ትምህርት፣ ኢንቨስትመንትና ሌሎችም ዘርፎች የዲያስፖራው ማህበረሰብ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታልም ነው ያሉት። አክለውም አገራቸውን ማገዝ የሚገባ እንጂ ባልተፈቀደለት አግባብ በፖለቲካው ውስጥ መግባት የለበትም ያሉት አቶ ኢድሪስ፣ አሁን ያለው ህገ መንግስት ተሻሽሎ "ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራ በፖለቲካው መስክ ቀጥታ የመሳተፍ መብት እስከ ሚያረጋግጥ ድረስ በህግ በማይፈቀድ ጉዳይ ላይ ጊዜ ማባከን አይገባምም" ነው ያሉት አቶ ኢድሪስ። በተለያዩ የውጭ አገራት ኑሯቸውን ያደረጉ ከ3 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በውጭ አገራት እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም