የደቡብ ሱዳን የሰላም ተደራዳሪዎች በተወሰኑ ጉዳዮች ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተሰማ

110
ሰኔ 20/2010 የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪርና የተቃዋሚው ኃይል መሪ ዶክተር ሪክ ማቻር በካርቱም ባደረጉት ውይይት በተወሰኑ ጉዳዮች ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አል- ዲርዲሪ ሞሀመድ አህመድን ዋቢ አድርጎ ቢቢሲ እንዳስነበበው ሁለቱ መሪዎች “በተወሰኑ ጉዳዮች” ላይ ተስማምተዋል፡፡ ስምምነቱን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎች ዛሬ ይፋ እንደሚደረጉም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ በሁለቱ መሪዎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ በሀገሪቱ የተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት  በሺዎች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፤ ከአራት ሚሊዮን የሚልቁትን ደግሞ አፈናቅሏል፡፡ የሰላም ድርደሩ በምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) አማካኝነት የሚካሔድ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ሁለቱ መሪዎች ከሁለት ዓመት በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ፊት ለፊት ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ ቢቢሲ የአፍሪካ መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሶ እንዳስነበበው ደግሞ ሁለቱ መሪዎች  ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም