ኢትዮጵያ አዲሱን የቡና መለያዋን የሚያስጠብቁ ስራዎች ያስፈልጓታል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ አዲሱን የቡና መለያዋን የሚያስጠብቁ ስራዎች ያስፈልጓታል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 01/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የተለያዩ አይነት ቡናዎቿን በአንድ ስም ወደ ዓለም ገበያ ለማስገባት ይፋ ያደረገችውን መለያ የሚያስጠብቁ የጥራትና የቅንጅት ስራዎች እንደሚያስፈልጓት ተገለጸ። በአረቢካ 'ሲ' ቡና መገኛነት ለዘመናት በዓለም የምትነሳው ኢትዮጵያ የተለያየ ጣዕም ያላቸው ቡናዎቿን በራሷ መለያ ባለማስተዋወቋ የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ አይደለችም። በቅርቡ ግን ቡናዬን መለያ ካላቸው አገራት ጋር ተቀላቅሎ ከመሸጥ ይታደጋል፤ በዓለም ገበያም ተወዳዳሪ ያደርጋል ያለችውን አገራዊ የቡና መለያ በአዲስ አበባ በተዘጋጀው 2ኛው ዓለም አቀፍ የቡና ፌስቲቫል ላይ አስተዋውቃለች፡፡ መለያው ኢትዮጵያ የቡና መገኛ የመሆኗን ታሪክ በምስል ያጣቀሰና "የኢትዮጵያ ቡና" የሚል ጽሁፍ ያለው ነው። በቡና ክፍለ ኢኮኖሚ ግብይትና ግብርና ላይ ተሳትፎ ያላቸው አካላት የአገራዊ መለያው ይፋ መሆን ለዘርፉ እድገት የራሱ ድርሻ ቢኖረውም መለያውን በመልካም የሚያስተዋውቁ ተጨማሪ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። በቡና እርሻና በወጪ ንግድ የተሰማሩት የዳዊ እርሻ ልማት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ወርቁ አንዳ፡- ምንም እንኳን አዲሱ መለያ በተለይ በዘርፉ ለተሰማሩ አካላትና ለአገር ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ ከፍተኛ ቢሆንም ባለድርሻ አካላቱ በምርት ጥራት ላይ ካልሰሩ ጥቅም እንደሌለው ነው አቶ ወርቁ ያስረዱት። የኢትዮጵያን ቡና ለዓለም የማስተዋወቅ ስራ የሚሰራው የኢትዮ ጋባና ድርጅት ተወካይ ወይዘሮ ሜሮን ተስፋዬም የእስካሁኑ የጥራትና የክፍያ ችግር በአገራዊው መለያ ይፈታል ብለው ያምናሉ። ለቡና መገኛውና ይህንም በማስተዋወቅ ተጠቃሚነትን ለማስፋት እየሰራ ላለው የደቡብ ክልል የመለያው ይፋ መሆን የሚያስገኘውን ጠቀሜታ የሚገልጹት የክልሉ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ባለሙያው አቶ አብርሃም አስታጥቄ ናቸው። አስተያየት ሰጪዎቹ አገራዊ መለያው ፍትሃዊ የቡና ንግድ ተጠቃሚነትን ለማምጣት የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ነው የገለጹት፡፡ ከአመራረቱ እስከ ግብይት ስርዓቱ ያለውን ሂደት ዓለም በደረሰበት ቴክኖሎጂ ለማድረስ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ተወዳዳሪ ምርት ለዓለም ለማቅረብ ዕድል የሚሰጥም ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢዋ 30 በመቶውን የምታገኘው ከቡና ነው።