የስራ እድል ፈጠራው በብድር አቅርቦት እጥረት የተፈለገውን ውጤት አላስገኘም - ኢዜአ አማርኛ
የስራ እድል ፈጠራው በብድር አቅርቦት እጥረት የተፈለገውን ውጤት አላስገኘም
ባህርዳር (ሰቆጣ ) ዲላ፣ የካቲት 1/ 2012( ኢዜአ ) በሰሜን ወሎ ዞን ለ30 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል ሲፈጠር በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርና በጌዴኦ ዞኖች ደግሞ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች በብድር አቅርቦት እጥረት መቸገራቸውን ገለፁ። በሰሜን ወሎ ዞን ወላጆችን በማሳተፍ ባለፉት ስድስት ወራት በተካሄደው እንቅስቃሴ ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች አዲስ የስራ እድል መፈጠሩን የዞኑ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ መምሪያ አስታውቋል። በመምሪያው የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቡድን መሪ አቶ አጽብሐ ከበደ እንደገለጹት በዞኑ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ ነው። ወላጆች ለልጆቻቸው የገንዘብ፣ የመስሪያና መሸጫ ቦታ፣ ንብረታቸውን በዋስትና በማስያዝና የመስሪያ ገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በስራ እድል ፈጠራው እንዲሳተፉ ተደርጓል። በዘንድሮው ዓመት በዞኑ ስር በሚገኙ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች 80ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ በግማሽ ዓመቱ ከ30 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተፈጥሯል። መንግስት ከ17 ሚሊየን ብር በላይ ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ ደጋፊ ለሌላቸው 604 ኢንተርፕራይዞችና አንቀሳቃሾች ብድር መሰጠቱን ተናግረዋል። የስራ እድሉን መፍጠር የተቻለውም በመንግስትና በግል ድርጅቶች እንዲቀጠሩ በማድረግና በማህበራት ተደራጅተው በብሎኬት፣ በአሸዋና ድንጋይ ማምረት፣ በእንጨትና ብረታ ብረት ስራ፣ በእደ ጥበብ፣ ምግብ ነክና በሌሎች ተያያዥ መስኮች በማሰማራት ነው። የስራ አድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል የወልድያ ከተማ ነዋሪ ወጣት ተስፋዬ አዳነ በሰጠው አስተያየት ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን በእህል ወፍጮና በተሽከርካሪ መለዋወጫ ንግድ መሰማራታቸውን ተናግሯል። መንግስት በመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ 646 ሺህ ብር ብድር ማግኘታቸውን ጠቅሶ በቀጣይ በሚያገኙት ትርፍ የራሳቸውን ህይወት ከመምራት ባሻገር ብድራቸውን ለመመለስ እየሰሩ መሆኑንን ገልጿል። ሌላው የከተማዋ ወጣት ዳዊት ቢሰጥ በበኩሉ መንግስት በሰጣቸው 810 ሺህ ብር ከ10 ጓደኞቹ ጋር በመሆን ከዓመት በፊት በወተት ልማት ስራ መሰማራታቸውን ገልጿል። በተበደሩት ገንዘብም የውጭ ዝርያ ያላቸውን 12 የተዳቀሉ ላሞች በመግዛት ወደ ስራ በመግባታቸው አሁን በቀን 80 ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብ ወርሃዊ ገቢያቸውን እስከ 60 ሺህ ብር ማድረስ መቻላቸውን ተናግሯል። በሌላ በኩል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርና በጌዴኦ ዞኖች በማህበር የተደራጁ ወጣቶች በቂ የብድር አቅርቦት ባለመኖሩ ስራቸውን በሚፈለገው መጠን ማስፋፋት እንዳልቻሉ ተናግረዋል። የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ወጣቶች እንደገለፁት በጥቃቅንና አነስተኛ የስራ ዘርፎች ለመሰማራት ብንደራጅም በብድር አቅርቦት ማጣት ምክንያት ወደ ስራ መግባት አልቻልንም ሲሉ ቅሬታ አሰምተዋል። በዞኑ አበርገሌ ወረዳ የኒረቃቅ ከተማ ነዋሪ ወጣት ወልዴ ኪሮስ በሰጠው አስተያየት ካለፈው ዓመት ጀምሮ አራት ሆነው በመደራጀት በጥራጥሬ ንግድ ለመሰማራት ቢፈልጉም በብድር አቅርቦት ማጣት ምክንያት እስከ አሁን ድረስ ወደ ስራ መግባት አልቻሉም። ለብድር የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን አሟልተው የ800 ሺህ ብር ቢዝነስ ፕላን አሰርተው ቢያቀርቡም በወረዳው አማራ ብድር እና ቁጠባ ቅርንጫፍ እንዳልተፈቀደላቸው ገልጿል። ወጣት ታደሰ አምባየ በበኩሉ ከተከዜ ሃይቅ የሚገኘውን የአሳ ምርት ለማከፋፈል አምስት ሆነው ቢደራጁም በብድር አቅርቦት እጥረት ወደ ስራ አልገባንም አለ። የብድር አቅርቦቱ እንዲመቻችላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም በማያውቁት ምክንያት ጠብቁ ከማለት ውጪ ችግራቸው ተረድቶ መፍትሔ የሚሰጣቸው አካል እንዳላገኙ ወጣቶቹ ተናግረዋል። አምስት ሆነው በቡሎኬት ማምረት ተደራጅተው በገንዘብ እጥረት ወደ ስራ መግባት እንዳልቻሉ የገለፀው ደግሞ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ ወጣት ደስታ ሙላው ነው። የብድር አቅርቦቱ በፍጥነት ሊመቻችላቸው እንደሚገባ የጠየቀው ወጣቱ መንግስት በብድር አቅርቦት ዙሪያ የሚስተዋለውን የአሰራር ችግር ሊፈታ ይገባል ነ ያለ። የብሄረሰብ አስተዳደሩ ቴክኒክና ኢንተርፕራይዞች መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ አብድርህማን መኮንን ስለጉዳዩ ተጠይቀው ቀድሞው ብድር የወሰዱ ወጣቶች መመለስ የሚገባቸውን ገንዘብ ባለመመለሳቸው አዲስ ለተደራጁ ወጣቶች ተጨማሪ ብድር መስጠት አስቸጋሪ መሆኑን አስረድተዋል። ባለፉት ስድስት ወራት ከ13 ሺህ በላይ ስራ ፈላጊዎችን ወደ ስራ ለማስገባት ቢታቀድም በብድር አቅርቦት እጥረት ምክንያት ስኬታማ ማድረግ እንዳልተቻለ አስረድተዋል። የስራ እድል ፈጠራ ጉዳይ የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳ በመሆኑ ችግሩን በመገምገም የተሰራጨውን ብድር አመራሩ ተቀናጅቶ እንዲያስመልስና ችግሩ እንዲፈታ አቅጣጫ ተቀምጦ ስራ መጀመሩን ገልፀዋል። የተዘዋዋሪ ብድር ስርጭት መቆም በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚዎች ስራን በቅንጅት ተናብቦ ባለመስራት የመጣ ችግር ነው የሚሉት ደግሞ የአማራ ብድርና ቁጠባ የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ካሳ ናቸው፡፡ ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ ለ1 ሺህ 611 ኢንተርፕራይዞች ከ79 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ማሰራጨት መቻሉን አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ ብድር ከወሰዱት ኢንተርፕራይዞች ውስጥ 145 ኢንተርፕራይዞች በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ እንደማይገኙ ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገውም አመላክተዋል፡፡ ከተሰራጨው ብድር ውስጥም እስካሁን ማስመለስ የተቻለው 25 ሚሊዮን ያህሉን ብቻ መሆኑን ጠቅሰው ብድር አለመመለሱ ደግሞ አዳዲስ ብድር ለመስጠት አልተቻለም ብለዋል። በተመሳሳይ መልኩ በጌዴኦ ዞን በገጠር የሥራ እድል ፈጠራ የተደራጁ ወጣቶች የብድር አቅርቦት ችግር በስራቸው ላይ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል ። በዞኑ ከ18 ሺህ በላይ ስራ አጦች የስራ እድል ለመፍጠር የልየታ ስራ መሰራቱ ተጠቁሟል። በዞኑ ወናጎ ወረዳ ነዋሪ የሆነው ወጣት ጀማል ሾጠና እንዳለው ከሶስት አመት በፊት ከ5 ጓደኞቹ ጋር በመሆን በዶሮ እርባታ ስራ መሰማራታቸውን ይገልፃል። 6 ሺህ ብር በመቆጠብ 42 ሺህ ብር ብድር ወስደው ወደ ስራ በመግባት ብድራቸውን በወቅቱ ከመመለስ ባለፈ አጠቃላይ ካፒታላቸውን ከ300 ሺህ ብር በላይ ማድረሳቸውን ተናግሯል። ይሁንና የስራ ዘርፍ ቀይረው ከብት በማድለብ ለመሰማራት ከ6 ወር በፊት የብድር ጥያቄ ቢያቀርቡም ማግኘት ባለመቻላቸው በስራችን ላይ ጫና አሳድሯል ነው ያለው። በይርጋጨፌ ወረዳ በቡና ችግኝ ማፍላት ተደራጅተው ወደ ስራ በገቡ አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ተስፋ ሰጪ ውጤት እያገኙ መሆናቸውን የገለፀው ደግሞ የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ተረፈ ለማ ነው ። ተጨማሪ ብድር ጠይቀው ስራቸውን ማስፋፋት ቢፈልጉም የጠየቁትን ገንዘብ ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግሯል ። በጌዴኦ ዞን ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ የገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ ልማት ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ መስፍን አለማየሁ በጉዳዩ ዙሪያ ተጠይቀው ከዚህ ቀደም ለማህበራት የተሰራጨ ከ192 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር አለመመለሱ ተጨማሪ ብድር ለማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።