ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ ለህግ ትምህርት ጥራት መሻሻል ትኩረት ሊሰጥ ይገባል አለ

ጎባ /ኢዜአ/ ጥር 30/2012 በሀገሪቱ የተሻለ የፍትህ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ለህግ ትምህርቱ ጥራት ማሻሻል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የፌዴራል የፍትህና ህግ ምርምርና ሥልጠና ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡ ኢንስቲትዩቱ  ”በኢትዮጵያ የህግ ትምህርት ጥራትን በማጠናከር ለተሻለ ፍትህ“ በሚል መሪ ሀሳብ ከመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር  ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ባሌ ጎባ ተካሄዷል፡፡

በመድረኩ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክትር አቶ ተስፋለም ይህደጎ እንደገለጹት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት ማስፈን የሚቻለው የህግ የበላይነት መረጋገጥ ሲቻል ነው።

ይህንን እውን ለማድረግም ህዝቡ በፍትህ ዘርፉ ላይ የሚያሰማውን ቅሬታ ለመፍታት  በህግ ትምህርት ቤቶችና ፍትህ ተቋማት መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

የተሻላ የፍትህ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በህግ ትምህርት ቤቶች የሚሰጠውን የህግ ትምህርት ጥራትን በማሻሻል ላይ ትኩረት ሊሰጠው  እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በተለይም በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በጥናት ለመለየት በሶስት የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናታዊ ምርምሮችን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ የህግ ትምህርት ቤቶች "ኮንሰርቲየም " ሰብሳቢ አቶ አበበ አሰፋ በበኩላቸው በሀገሪቱ  በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚታዩ ውስብስብ ችግሮች መፍታት  የሚቻለውም የህግ ትምህርት ቤቶች የራሳቸውን ሚና ሲወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን ችግር ለመፍታት ከአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጋር የተጣጣመ የህግ ስርዓተ ትምህርት ክለሳና ሌሎች ማሻሻያዎችን በማዘጋጀት ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት መላኩን ተናግረዋል፡፡

በህግ ትምህርት ቤቶች የሚሰጠውን ትምህርት ጥራት ለማስጠበቅም የመውጫ ፈተና የመዘጋጀትና ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የተማሩትን በተግባር እንዲተገብሩ ሀገር አቀፍ የምስለ-ችሎት ውድድር በየዓመቱ እንደሚዘጋጅ ጠቁመዋል፡፡

ኮንሰርቲየሙ በዩኒቨርሲቲ የህግ መውጫ ፈተናዎች ላይ ቅሬታ ለነበራቸው 365 ተማሪዎችን በማጣራት መፍታት መቻሉን ያስረዱት አቶ አበበ ፤በቀጣይም በተደጋጋሚ የመውጫ ፈተናዎችን ወስደው ማለፍ ያልቻሉ ተማሪዎች ለቀጣይ ፈተና ለማዘጋጀት  እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

" ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል"ያሉት ደግሞ  የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ ሰለሞን ግርማ ናቸው።

የህግ ተማሪዎችም  ፍትህ ለማግኘት ለተቸገሩ  የህብረተሰብ ክፍሎች እየሰጡ የሚገኘው ነጻ የህግ አገልግሎት የተግባር ልምምድ በመሆን ጭምር በዘርፉ ጥራት ለማምጣት እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡

"ዩኒቨርሲቲው ከሚሰጣቸው ነፃ የህግ አገልግሎት መካከልም የምክር፣ ጥብቅና የመቆም፣ ክስ የመመስረት እንዲሁም ሰነዶችንና ማመልከቻዎችን የማዘጋጀት ስራዎች ይገኙበታል "ብሏል፡፡

ባለፉት አምስት ወራት ውስጥም 400 የሚጠጉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዩኒቨርሲቲው በሚሰጠው ነጻ የህግ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ የህግ ትምህርት ቤቶች ኮንሰርቲየም 32 የመንግስትና የግል የህግ ትምህርት ቤቶችን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን የህግ ትምህርት ጥራትን በማሻሻል ብቁ የህግ ባለሙዎችን ማፍራት ለህግና ፍትህ ስርዓቱ መሻሻል ዓላማ አድርጎ እየሰራ መሆኑን በመድረኩ ተገልጿል፡፡

የምክክር መድረኩ ከጥር27/2012ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት የተካሄደ ሲሆን በሀገሪቱ ከሚገኙ ሁሉም  የህግ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ ተወካዮች  ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም