ቀጥታ፡

ኤርትራ ልዑኳን ወደ ኢትዮጵያ መላኳ ታሪካዊ ክስተት ነው-ምሁራን

አዲስ አበባ ሰኔ 19/2010 ኤርትራ ልዑኳን ወደ ኢትዮጵያ መላኳ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን  የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ምሁራን ገለጹ። የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ላለፉት 20 ዓመታት የነበረውን 'ሞት አልባ ጦርነት ' ለመቋጨት የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ ፓኬጁን ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያሰ አፈወርቂ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ወደ አዲስ አበባ የልዑካን ቡድን እንደሚልኩ በኤርትራ  የሰማዕታት በዓል ላይ ባስተላለፉት መልእክት መሰረት ልዑካን ቡዱኑ ዛሬ አዲስ አበባ ገብቷል። ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ እንደገለጹት፣ ከሁለቱም ህዝቦችና ከአከባቢው አገሮች ዘላቂ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መረጋገጥ አኳያ የኤርትራ መንግሥት የልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር ለዓመታት የቆየውን አለመግባባት በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት አዲስ አበባ መግባታቸው "የአዲስ ምዕራፍ ክስተት  ሆኖ ተመዝግቧል" ። የሁለቱ አገራት ከፍተኛ የልዑካን ቡድንም ወደ ዝርዝር ጉዳያቸው ከመግባታቸው በፊት አንዱ የአንዱን የሰላም ፍላጎት፣ የመተዋወቅ፣ የሚያጠራጥሩ ስጋቶችን የማስወገድና የመተማመን ሁኔታዎች የሚፈጠሩበት ግኑኝነት እንደሚሆን ተናግረዋል። እንደ እህትማማች አገሮችና  በደም፣ በባህል፣ በቋንቋና በታሪክ የተሳሰሩ ህዝቦች አንፃር የሰላም ድርድሩ የዘገየ ካልሆነ በስተቀር በአሁኑ ወቅት የሰላም ሂደቱ መጀመሩ አስፈላጊ ነው ብለዋል። በመሆኑም የሰላም ድርድሩን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ሁለቱም መንግስታት የውል ስምምነቶችን ማስቀመጥ ይገባቸዋል ብለዋል ፕሮፌሰሩ። ሁለቱም አገሮች "ባለፉት 20 ዓመታት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኪሳራ ያደረሰ ግጭት አሳልፈዋል" ያሉት ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት(ኢጋድ) የፀጥታና ደህንነት  ፕሮግራም ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙልነህ ናቸው። የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈው ሳምንት በሰማዕታት ክብረ በዓል ላይ በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ልዑካን እልካለሁ ያሉትን ቃል ማክበራቸውን አድንቀዋል፡፡ ሁለቱም አገሮች ከሚለያያቸው ይልቅ በጣም የተቆራኙ ህዝቦች በመሆናቸው በመካከላቸው ሶስተኛ ገለልተኛ ወገን እንደማያስፈልግ ሊያሰምሩበት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ይገባኛል ግጭት ግንቦት 4 ቀን 1990 ዓ.ም መከሰቱ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም