በድሬዳዋ-ደወሌ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ16 ሰዎች ህይወት አለፈ

ድሬዳዋ ጥር 30/2012፡- በድሬዳዋ-ደወሌ የክፍያ ኮንክሪት አስፋልት መንገድ ላይ ዛሬ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የ16 ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ። አደጋው የደረሰው ዛሬ ከንጋቱ 11 ሰዓት አካባቢ ከድሬዳዋ-ደወሌ-ጅቡቲ በሚወስደው የክፍያ መንገድ ላይ ነው። ከድሬዳዋ ወደ ጅቡቲ መንገድ ይጓዙ የነበሩ  ሶስት ሚኒባሶች እና ከጅቡቲ ወደ ድሬዳዋ በሚመጡ ሁለት "ዩሮ ትራከሮች " መካከል ላስዴሬ በተባለ ሥፍራ በመጋጨታቸው አደጋው መድረሱን በሶማሌ ክልል የሲቲ ዞን የትራፊክ ፖሊስ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ጉሌድ ገዲድ ለኢዜአ ገልጸዋል። በዚህም ህይወታቸው ካለፈው ሌላ  በ12 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ድሬዳዋ ድል ጮራ ሆስፒታል ተወስደው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል። አደጋው ከፍጥነትና ከትዕግስት ማጣት ጋር የሚያያዝ ቢሆንም ጉዳዩ  እየተጣራ ነው ብለዋል። በድሬዳዋ-ደወሌ የክፍያ መንገድ ላይ ተደጋጋሚ የተሽከርካሪ  አደጋ እየደረሰ በመሆኑ አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስበዋል። የኢዜአ ሪፖርተር የተረፉት ተጎጂዎች በድሬዳዋ ድል ጮራ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ ሲደርግላቸው በስፍራው መመልከቱን ገልጿል። በሆስፒታሉ  የድንገተኛ ህክምና ክፍል አስተባባሪ ነርስ ዮሃንስ በስብሃት ወደ ሆስፒታሉ ተጎድተው ከመጡት መካከል ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት አንድ ሰው ህክምና እየተደረገለት ህይወቱ ማለፉን ገልፀዋል፡፡ የተቀሩት ግን በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ለሪፖርተራችን ተናግረዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ሙሣ ጠሃ ፣ የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ እና ሌሎች አመራሮች እንዲሁም የሲቲ ዞን አመራሮች በስፍራው ተገኝተው ተጎጂዎችን አፅናንተዋል፡፡ በአደጋው ሳቢያ ለሰዓታት ተዘግቶ የነበረው የድሬዳዋ-ደወሌ የክፍያ መንገድ በአሁኑ ሰዓት ለትራፊክ ክፍት ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም