ቀጥታ፡

የሰላምና ጸጥታ ችግር የአህጉሪቱን የምግብ ዋስትና አደጋ ላይ ጥሏል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 29/2012 የሰላምና ጸጥታ ችግር የአፍሪካ አህጉርን የምግብ ዋስትና አደጋ ላይ መጣሉ ተገለጸ። ከአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ በህብረቱ አዳራሽ የተለያዩ ውይይቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ። ''እጅ ለእጅ ተያይዘን ወዳጅነታችንን በማጠናከር የአፍሪካን ሰላምና ምግብ ዋስትና እናረጋግጥ'' በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስትር፣ የህብረቱ የገጠር ኢኮኖሚና ግብርና ኮሚሽነር፣ የአለም የእርሻና ምግብ ድርጅትን ጨምሮ የዓለም አቀፍና የአህጉሪቱ ተወካዮች ታድመዋል። በዚሁ ጊዜ አፍሪካን የምግብ ዋስትናዋንና የስርዓተ ምግቧን እንዳታረጋግጥ ካደረጉ ምክንያቶች ዋነኛው የሰላምና ጸጥታ ችግር ነው ተብሏል። አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ረሃብን በማጥፋት ዘላቂ የልማት ግቦቻቸውን እንዳያሳኩ ያደረገውም ይህ ያለመረጋጋት መሆኑ ተነስቷል። በአገሮቹ በሚነሱ የተለያዩ ግጭቶች ምክንያት የእርሻ ቦታዎች ጉዳት ይደርስባቸዋል። በርካታ ዜጎችም ለድህነትና ለረሃብ ይዳረጋሉ ተብሏል። የህብረቱ የገጠር ኢኮኖሚና ግብርና ኮሚሽነር ጆሴፋ ሊዮኔል ሳኮ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ያለ ሰላም የምግብ ዋስትና አይረጋገጥም ያለ ምግብ ዋስትናም ሰላም አይመጣም። አንዱን ከአንዱ ነጥሎ ማየት የማይታሰብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተለይም የአፍሪካ መሪዎች ግጭትን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚቻልባቸውን መንገዶች ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው ብለዋል። አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ላይ በሚያጋጥመው ግጭት ምክንያት ዜጎች በቂ ምግብ ባለማግኘታቸው ለስደትና ለሞት የሚዳረጉ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም እ.ኤ.አ በ2030 አህጉሪቱን ከድህነት ለማውጣት የተያዘው አጀንዳ ውጤታማ እንዳይሆን ተጽዕኖ አለው ብለዋል። ከሰላምና ጸጥታ ጎን ለጎን የአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካ የምግብ ዋስትናዋን እንዳታረጋግጥ ማድረጉን ገልጸው፤ መሪዎች ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ምሁራንና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ከግጭት ነጻ አህጉር ለመፍጠር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም