ቀጥታ፡

ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ህብረት የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚቴ ሊቀመንበርነትን ከጋቦን ተረከበች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 30/2012 ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ህብረት አገሮች መሪዎችና መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚቴ (ካሆስክ) ሊቀመንበርትን ዛሬ ከቦን ተረክባለች። ኮሚቴው መደበኛ ስብስባውን ዛሬ በህብረቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል። ኮሚቴው ስብሰባውን ያደረገው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ነገ በሚጀመረው 33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ የሚያቀርቡት የአየር ንብረት ለውጥ ሪፖርት አጀንዳ ላይ ለመወያየትና ለመገምገም ነው። በስብሰባው ላለፉት ሁለት ዓመታት ኮሚቴውን በሊቀመንበርነት ስትመራ የቆየችው ጋቦን ሊቀመንበርነቷን ለደቡብ አፍሪካ አስረክባለች። የጋቦን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሌን ክላውዴ ቢሊ ባይንዜ ለደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ የኮሚቴ ሊቀመንበርነቱን አስረክበዋል። ደቡብ አፍሪካ ለቀጣይ ሁለት ዓመት ኮሚቴውን በሊቀመንበርነት ትመራለች። በኢትዮጵያ የጋቦን አምባሳደር ኢሞንጎ ሄርማን ኮሚቴው የአፍሪካ አገሮች በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ አንድ ድምጽ እንዲኖራቸውና በጉዳዩ ላይ ተቀናጅተው እንዲሰሩ የማመቻቸት አላማ እንዳለው ለኢዜአ ገልጸዋል። አፍሪካውያን በአሁኑ ሰአት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በአንድ ድምጽ አቋማቸውን እያንጸባረቁ እንደሚገኝና ይሄም አፍሪካን በዓለም አቀፍ መድረኮች ተሰሚ እያደረጋት መሆኑን ተናግረዋል። አፍሪካ በአሁኑ ሰአት የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ለጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጡትና የአየር ንብረት ለውጡ የሚያስከትለውን ተጽእኖ መቋቋም እንዲችሉ ስትራቴጂዎችን ቀርጻ እየሰራች ነው ብለዋል። የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚቴው ለነገው ሰብስባ የሚቀርበውን አጀንዳ ከመመልከት ባለፈ በስኮትላንድ ርዕሰ መዲና ግላስኮው ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ከወዲሁ የምታንጸባርቃቸው ሀሳቦች ላይ እንደመከረም ጠቅሰዋል። በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ በበኩላቸው ኮሚቴው የአፍሪካ አገሮች በአየር ንብረት ለውጥ በተደራጀና በቀተናጀ መልኩ ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ መድረክ የፈጠረ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ካላት ጠንካራ አቋም አንጻር አፍሪካውያን በትብብር እንዲሰሩ ለኮሚቴውና ለአገሮች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመከላከል የችግኝ ዛፍ ተከላ፣ የተፋሰስ ልማት ስራዎችና ታዳሽ ሃይል አማራጭን መጠቀም ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች እንደሆነም አመልክተዋል። የአፍሪካ ህብረት መሪዎችና መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚቴ (ካሆስክ) እ.አ.አ በ2012 የተቋቋመ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ 15 አባላት አሉት። ግብጽ የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚቴው የመጀመሪያ ሊቀመንበር ነበረች።33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ነገና ከነገ በስቲያ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም