ቀጥታ፡

የኢትዮ-ካናዳ የቢዝነስ ፎረም እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ጥር 30/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ እና የካናዳ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በቢዝነስ ፎረሙ 20 የካናዳ እና 100 የኢትዮጵያ ባለሃብቶች ተሳታፊ ናቸው። ካናዳዊያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በንግድ ዘርፍ ከኢትዮጵያዊያን አቻዎቻቸው ጋር በጋራ መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ  እየመከሩ ነው። የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ቱሩዶ እና የካናዳ የቢዝነስ ልዑካን ቡድን አባላት በትናትናው ዕለት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል። በካናዳው የንግድ ኮሚሽነር ሲንዲ ኢቭ ቦራሳ የተመራው የቢዝነስ ልዑክ ከግብርና፣ ከኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ እና ከሌሎችም ዘርፎች የተወጣጣ ነው። የንግድ ልውውጥ መድረኩ የሁለትዮሽ ትብብርና የልምድ ልውውጥ በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል። የሁለቱ አገራት የንግድ ልውውጥ መጠን በአውሮፓዊያኑ የ2018 ዓመት 170 ሚሊዮን ዶላር ነበር። ከዚህ ውስጥ 130 ሚሊዮን ዶላሩ ካናዳ ወደ ኢትዮጵያ ከላከችው ምርቶች ያገኘችው ነው። በዚሁ ዓመት ካናዳ በኢትዮጵያ የነበራት ቀጥታ የኢንቨስትመንት መጠን ደግሞ 174 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ተመዝግቧል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም