የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ተጠናቀቀ

67

አዲስ አበባ፤ ጥር  29/2012(ኢዜአ) ከትናንት ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው 36ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል። ’’የጦር መሳሪያ ድምጽን በማጥፋት ለአፍሪካ ዕድገት ምቹ ሁኔታ መፍጠር’’ በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላለፉት ሁለት ቀናት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክሯል።

ምክር ቤቱ የቀረበለትን ረቂቅ አጀንዳና የውሳኔ ሃሳብን መርምሮ የገመገመ ሲሆን የካቲት 1 እና 2 ቀን 2012 ዓ.ም ለሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ያቀርባል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ሌሎች ባለስልጣናት በተገኙበት የተካሄደው ስብስባ ላይ የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ ሪፖርትና የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በዝግ ውይይት አድርገዋል።

ሰላምና መረጋጋት፣ የአፍሪካ ህብረት እያከናወናቸው ያሉ የማሻሻያ ስራዎች፣ የአፍሪካ ህብረት የፋይናንስ ሁኔታ፣ የአፍሪካ ህብረት የመዋቅር ማስተካከል ስራዎችና የህብረቱ አባል አገሮች በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላቸውን ተሰሚነትና ተሳትፏቸውን ማሳደግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እየተከናወኑ ያሉ የትብብር ስራዎች የሁለት ቀናት የውይይት አጀንዳዎች ነበሩ።

በመድረኩ ላይ ከህብረቱ አባል አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተጨማሪ የኮሚሽኑ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም