ቀጥታ፡

የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ለማቃለል መንግስት ከዲያስፖራው ጋር ተቋማዊ ግንኙነት ሊመሰርት እንደሚገባ ተጠቆመ

ጥር 29/2012 (ኢዜአ) እንደ አገር እያጋጠመ ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለል መንግስት ከዲያስፖራው ጋር ተቋማዊ ግንኙነት ሊመሰርት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር አስታወቀ። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ያላት የመጠባበቂያና የውጭ ምንዛሬ ክምችት በቂ እንዳልሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገለጽ ይደመጣል። የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉትም ከችግሩ ለመውጣት የወጪ ንግድ ላይ በርትቶ መስራት አንድ አማራጭ ነው። የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኢድሪስ መሀመድ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት እያጋጠመ ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለል መንግስት ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር ተቋማዊ ግኙነት መመስረት ይኖርበታል። ''መንግስት በተለያየ ጊዜ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ያለው ግንኙነት በተደራጀ አግባብ ስላልሆነ ቀጣይነት ያለው ግንኙነት ሲመሰረት አይታይም" ብለዋል። ላለፉት አሥር ዓመታት መንግስት በእርዳታና በብድር ከሚያገኘው ገቢ በተጨማሪ ከወጪ ንግድ ዶላር የሚያገኝበት ሁኔታ ቢኖርም ከዲያስፖራው የሚገኘው ገቢ ከወጪ ንግዱ አንጻር ሲታይ የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ባለፉት 5 ዓመታት ከወጪ ንግዱ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር፤ ከዲያስፖራው ወደ አገር ውስጥ ከተላከ ገንዘብ ደግሞ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን አቶ ኢድሪስ በማሳያነት ጠቅሰዋል። "ይህም መንግስት በዲያስፖራው ላይ በቁርጠኝነት ቢሰራ ኪዚህም የተሻለ ገቢ ማግኘትና የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ማቅለል እንደሚቻል ያሳያል" ሲሉ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር የቦርድ አማካሪ ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ በበኩላቸው "መንግስት ከሁሉ አስቀድሞ ዲያስፖራው በአገሩ እንዲተማመንና በኢንቨስትመንት እንዲሳተፍ በገጽታ ግንባታ ላይ ሰፊ ሥራ መስራት አለበት" ብለዋል። እንደ አማካሪው ገለጻ በውጭ የሚኖር ትውልደ ኢትዮጵያዊ ገንዘቡን በአውሮፓ ባንኮች ቢያስቀምጥ ሊያገኝ የሚችለው ወለድ 1 ነጥብ 1 በመቶ  ነው። ይሁንና ወደ አገር ቤት ልኮ ቢያስቀምጥ 8 ነጥብ 5 በመቶ ወለድ ያገኛል። "ገንዘቡን በአገር ውስጥ ማስቀመጥ ለአገር ማበደርና ለራስም መቆጠብ ነው" ያሉት ኢንጂነር ተረፈ  ዲያስፖራው ለአገሩ አበድሮ ለራሱም የሚቆጥብበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መንግስት በዲያስፖራው ላይ አተኩሮ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል። ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ሲያስቡ የአገሪቱ መጠባበቂያና የውጭ ምንዛሬ ክምችት ምን ይመስላል የሚለውን ከግምት እንደሚያስገቡ ያስታወሱት ኢንጂነር ተረፈ "ክምችቱን ለማሳደግ ዲያስፖራውን ተቋማዊ በሆነ መልኩ መጠቀም ያስፈልጋል" ብለዋል። እንደ ሕንድ፣ ቻይናና ደቡብ ኮሪያ ያሉ የባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት አገራት ለዛሬው የዕድገት ደረጃቸው የደረሱት ዲያስፖራ ዜጋቸውን ጭምር ተጠቅመው ስለሆነ ተሞክሯቸውን መውሰድ እንደሚያስፈልግ  ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም