ቀጥታ፡

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከተለያዩ አገሮች የስራ ሃላፊዎች ጋር የሁለትዮሽ ምክክር አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29/2012 (ኢዜአ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ከዴሞክራቲክ ኮንጎና ከታንዛንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያዩ።

ትናንት የተጀመረው 36ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ዛሬም እንደቀጠለ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከስብሰባው ጎን ለጎን በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ ገልጸዋል። አቶ ገዱ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ሚስ ረይም አል ሀሺሚ ጋር በነበራቸው ቆይታ አገሮቹ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር ላይ አላማ ያደረገ ውይይት አድርገዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ''ሁለቱ አገሮች አሁን ያላቸው ግንኙነት በጣም ጠንካራ እንደሆነና ይሄንንም ግንኙነት ከዚህ በበለጠ የላቀ ደረጃ ለማድረስ መስራት አለባቸው'' ብለዋል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥልም ጠይቀዋል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ሚስ ረይም አል ሀሺሚ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ሁሉን አቀፍ ማሻሻያ አድንቀው፤ አገራቸው ለኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ድጋፍና ትብብር አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እንዲቻል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቅሰው፤ በተጨማሪም በባህልና ቱሪዝም እና በሌሎች መስኮች ያላትን ግንኙነት እንደጠናክር ገልጸዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከዴሞክራቲክ ኮንጎ አቻቸው ሚስ ማሪ ቱምባ ንዜዛ ጋር በሁለትዮሽ፣ ክልላዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል። አገሮቹ የናይል ተፋሰስ አባል አገሮች በመሆናቸው በአባይ ወንዝ የአገሮቹ ህዝቦች በጋራ መልማት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ የሚያደርገውን በረራ እየጨመረ ከመጣው የተጓዥ ፍላጎት ጋር ለማጣጣም ተጨማሪ ውይይት ለማድረግም ወስነዋል። በተመሳሳይ አቶ ገዱ ከታንዛንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ፓላማጋምባ ጆን ካቡዲ ጋር በነበራቸው ቆይታ አገሮቹ የጋራ ኮሚሽን ስብስባ ማካሄድ በሚችሉበት ሁኔታና በናይል ተፋስስ ላይ በትብበር መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውንም አቶ ነቢያት ለኢዜአ ተናግረዋል።

የዴሞክራቲክ ኮንጎ መንግስት ኢትዮጵያ በአገሪቷ ለምታስገነባው ኤምባሲ ላቀረበችው ነጻ መሬትና በታንዛንያ ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለምታድረገው ድጋፍ አቶ ገዱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ሁለቱ አገሮች በአየር መንገድ፣ በኢንዱስትሪና በመሰረተ ልማት ላይ መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይም ውይይት አድርገዋል።

36ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባ ማምሻውን የሚጠናቀቅ ሲሆን በህብረቱ በኩል የሁለት ቀናት ውይይት ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም