የመሰረተ ልማት ጥያቄያችን ምላሽ እያገኘ ነው---በደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች

ደብረ ማርቆስ ሰኔ19/2010 በአካባቢያቸው ሲያነሱት የቆየው የመሰረተ ልማት ጥያቄ  ምላሽ እያገኘ መሆኑን በደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ በተያዘው የበጀት ዓመት 150 ሚሊየን በሆነ ወጪ የመንገድና ሌሎችም የመሰረተ ልማት ስራዎች በከተማው እንደተከናወኑ ተመልክቷል፡፡ በከተማው የቀበሌ ሶስት ነዋሪ ወይዘሮ ደለለች መርሻ ለኢዜአ እንደገለፁት ቀደም ሲል በአካባቢያቸው የውስጥ ለውጥ መንገድ ባለመገንባቱ በበጋ ወራት በአቧራ በክረምት ደግሞ በጭቃ ይቸገሩ ነበር። ችግሩ እንዲፈታላቸው ከሌሎች ነዋሪዎች ጋር በመሆን ጥያቄ ሲያነሱ መቆየታቸውን ጠቅሰው በተያዘው ዓመት የድንጋይ ንጣፍ  መንገድ እንደተሰረላቸውንው ተናግረዋል፡፡ በዚህም ለእግረኛው ምቹ ከመሆኑም በላይ  በተሽከርካሪ እንደልባቸው ለመግባትም ሆነ ለመውጣት እንደቻሉ አመልክተዋል፡፡ የቀበሌ አራት ነዋሪዋ  ወይዘሮብርቄ እንዳለ በበኩላቸው አካባቢያቸው አቋርጦ የሚያልፈው መንገድ በድንጋይ ንጣፍ በመሰራቱ ለሚተዳደሩበት አነስተኛ የንግድ ገበያ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። መንገድ እንዲሰራ በነበራቸው ፍላጎት ለግንባታው የሚውል አንድ ሺህ 500 ብር በጥሬ ገንዘብና የጉልባት ድጋፍ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ አካባቢያቸው ለጎርፍ ተጋላጭ የነበረ በመሆኑ  ከባድ ዝናብ ሲጥል መንገድ ጥሶ ወደ ቤታቸው በመግባት  በንብረታቸው ላይ ጉዳት ሲያደርስባቸው መቆየቱን የገለጹት ደግሞ የቀበሌ አምስት ነዋሪ አቶ ልኡል አደመ ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት ጎርፉ  እቃቤታቸው ውስጥ በመግባት ከሁለት ኩንታል በላይ የቀለብ ጤፍና ጥራጥሬ ከጥቅም ውጪ እንዳደረገባቸው አስታውሰው ዘንድሮ ግን  የውሃ ማፋሰሻ በመገንባቱ ከስጋት ነፃ መሆናቸውን አመልክተዋል። ነዋሪዎቹ እንዳሉት ለአስተዳደሩ ሲያነሱት የነበረው የመሰረተ ልማት ጥያቄያቸው አሁን ምላሽ እያገኘ  ነው፤ ልማቱም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ የከተማው  አስተዳደር ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን አገልግሎት  ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ዝግአለ ካሳ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ከ150 ሚሊዮን በር በላይ ወጪ በማድረግ 18 ኪሎ ሜትር የጎርፍ ማፋሰሻ ፣ አምስት ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ሰርተዋል፡፡ እንዲሁም ሰባት ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ጠረጋ እና ጠጠር ማልበስ፣ አንድ ድልድይና የስድስት  ኪሎ ሜትር የመንገድ ዳር ኤሌክትሪክ  መብራት ዝርጋታ  ስራዎች ተከናውነዋል። በተከናወኑት የልማት ስራዎችም ከ300 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ጊዜያዊ ስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ በልማት ስራው ህብረተሰቡ በጉልበት፣ በጥሬ ገንዘብ እና በቁሳቁስ ከ33 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ስራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በከተማው 70 ሚሊየን ብር በሚሆን  ወጪ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች እንደተከናወኑም ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም