ቀጥታ፡

ዲያስፖራው አገራዊ ሠላም ለማረጋገጥ ወደ ተግባር እንቅስቃሴ ይገባል

 አዲስ አበባ ( ኢዜአ) ጥር 29/2012 የዲያስፖራው ማኅበረሰብ የአገሩን ሠላም ለማረጋገጥ ከመናገር ባለፈ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኀበር አስታወቀ።

"ዲያስራው ለአገር ሠላም ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ ለዲያስፖራው ማኅበረሰብ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ የካቲት 3 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

 የመድረኩን መርሃ ግብር አስመልክቶ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኅበር ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም ስዩም እንደገለጹት ዲያስፖራው ማኅበረሰብ የአገሪቷን ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ ተግባራዊ ስራዎችን ለማከናወን እንቅስቃሴ ጀምሯል።

በመጪው የካቲት 3 በሚካሄደው ውይይትም ዲያስፖራው ለአገሩ ሠላምና መረጋጋት ምን ማበርከት እንዳለበት የሚያመላክቱ  ሃሳቦች በምሁራን የሚቀርቡ ይሆናል።

አገሪቷ ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ በኢንቨስትመንት፣ በጤና፣ በትምህርትና መሰል ዘርፎች መጠቀም የሚገባትን ያህል እድትጠቀም ሠላም ማስፈን ቀዳሚ ተግባር በመሆኑ ዲያስፖራው ተከታታይ ተግባራትን ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በመሆን እንደሚያከናውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኢድሪስ መሃመድ በበኩላቸው ዲስፖራው በሁለንተናዊ የአገር እድገት ተሳታፊነቱን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

በመሆኑም ዘላቂ ሠላም ሰፍኖ በውጭ አገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መዋዕለ ነዋያቸውን በአገራቸው እንዲያወጡ የተጀመሩት እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል ብለዋል።

በመድረኩ የጠዋት መርሃ ግብር ከየትኛውም ዓለም የመጣ ዲያስፖራ የማኅበሩ አባል ባይሆንም በውጭ አገር ነዋሪነቱን የሚያሳይ ፓስፖርት ያለው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ መካፈል እንደሚችል ተገልጿል።

በዕለቱ ከሠዓት በኋላ የዲያስፖራ ማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤ የሚካሄድ ሲሆን ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ማኅበሩን የሚመሩ አመራሮች የሚመረጡበትና ዝርዝር ውይይቶች እንደሚካሄዱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም