ቀጥታ፡

የሊጉ አራት የ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የቀን ለውጥ ተደረገባቸው

አዲስ አበባ፣ ጥር 29/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ13ኛ ሳምንት አራት ጨዋታዎች ላይ የቀን ለውጥ ተደርጓል። የሊጉ ጨዋታዎች ከነገ እስከ መጪው ሐሙስ ባሉት ቀናት ይካሄዳሉ። ከጨዋታዎቹ አራቱ ቀደም ብሎ ከተያዘላቸው መርሃ-ግብር ውጭ የቀን ለውጥ ተደርጎባቸዋል። የቀን ለውጥ ከተደረገባቸው ጨዋታዎች መካከል እሁድ ጨዋታቸውን ያደርጉ የነበሩት የሀዲያ ሆሳዕናና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ወደ ማክሰኞ ተሸጋግሯል። ለዚህም ምክንያቱ ሀዲያ ሆሳዕና ሁለት የሜዳ ላይ ጨዋታዎቹን በገለልተኛ ሜዳ እንዲያደርግ በመቀጣቱ በሃዋሳ ስታዲየም ጨዋታውን ያደርጋል። በተመሳሳይ ነገ ሊደረግ የነበረው የሃዋሳ ከተማና የጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ ወደ እሁድ ሲዘዋወር፤ እሁድ ይደረግ የነበረው የሲዳማ ቡናና የአዳማ ከተማ ጨዋታም ወደ ሰኞ ተሸጋግሯል። የኢትዮጵያ ቡናና የወልቂጤ ከተማ ጨዋታም እሁድ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረግ የነበረ ቢሆንም በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ምክንያት ወደ ሐሙስ የተዘዋወረ ጨዋታ ሆኗል። ነገ በዘጠኝ ሠዓት መቀሌ 70 እንደርታ ከፋሲል ከነማ በትግራይ ስታዲየም ይጫወታሉ። እንዲሁም እሁድ ከቀኑ ዘጠኝ ሠዓት ሀዋሳ ከተማ ከጅማ አባጅፋር፣ ባህርዳር ከተማ ከሰበታ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ ከስሁል ሽረ እንዲሁም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታዎቻቸውን ያደርጋሉ። ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ ሰኞ የሚከናወን ሲሆን፤ ሀዲያ ሆሳዕና ከወላይታ ድቻ ማክሰኞ ይጫወታል። ኢትዮጵያ ቡና ከወልቂጤ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታም ሐሙስ በ10 ሠዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይከናወናል። ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ23 ነጥብ ሲመራ፣ መቀለ 70 እንደርታና ፋሲል ከነማ በእኩል 22 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ይከተላሉ። ኢትዮጵያ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማና ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ከ14 እስከ 16ኛ ደረጃን ይዘው በሊጉ ግርጌ  ተቀምጠዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም