ቀጥታ፡

ከእስር የተፈቱ 75 ኢትዮጵያውያን ከታንዛኒያ ወደ አዲስ አበባ ይገባሉ

ጥር 29/2012 (ኢዜአ) ከህገ-ወጥ ስደት ጋር በተያያዘ በታንዛኒያ መንግስት ቁጥጥር ስር ውለው በተለያዩ እስር ቤቶች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን መካከል 75ቱ ዛሬ ሌሊት ከታንዛኒያ ተነስተው ነገ ጠዋት አዲስ አበባ እንደሚገቡ በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ አስታውቋል፡፡
 
እንደ ኢምባሲው ገለጻ በሀገሪቱ ታስረው የነበሩትን 1443 ዜጎችን ኢምባሲው በማስፈታት ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱ ነው ያስታወቀው።
 
ኢምባሲው ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሀገር እንዲመለሱ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ዜጎችን የመመለሱን ስራ በይፋ መጀመሩን አስታውቋል።
 
በአሁኑ ሰዓት ለመጀመሪያ ዙር ጉዞ ዝግጁ የሆኑ 75 ዜጎች ሙትዋራ ሉሉንግዌ ከሚባል እስር ቤት ተፈትተው ዳሬ ሰላም የደረሱ ሲሆን ነገ ከጠዋቱ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ይደርሳሉ።
 
በቀጣዩ ሳምንትም ከረበዕ ጀምሮ የተቀሩትን ዜጎችን የማጓጓዝ ስራው ይቀጥላል።
 
ዜጎችን ወደ ሀገር የመመለሱ ስራ በዋናነት በኢትዮጵያ መንግስት የሚከናወን ሲሆን ለ1443 ዜጎች የአየር ትኬት አቅርቦት የኢትዮጵያ መንግስት ያደርጋል።
 
የዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅትና የአውሮፓ ህብረት የሀገር ውስጥ መጓጓዣ በማቅረብና ወደ ሀገር ከተመለሱ በኋላ ባለው የመልሶ ሟቋቋም ስራ ውስጥ ይሳተፋሉ።
 
በዳሬ ሰላም ኤምባሲ መከፈቱን ተከትሎ እስከ አሁን ድረስ 1100 የሚሆኑ ዜጎች በተለያየ ወቅት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ የሚታወስ ነው።
 
ምንጭ፡በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም