ቀጥታ፡

የበሽታ አምጪ ተዋሲያን መስፋፋትና ከመድኃኒት ጋር መላመድ ችግርን ለመቀነስ እየተሰራ ነው

አዳማ  ሰኔ 19/2010 በሀገሪቱ እየተስፋፋ የመጣውን በሽታ አምጪ ተዋሲያን መስፋፋትና ከመድኃኒት ጋር የመላመድ ችግር ለመቀነስ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የእንስሳት መድኃኒት፣ መኖና አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ። ባለስልጣኑ ባካሄደው ፀረ-ተዋሲያን መላመድ የዳሰሳ ጥናት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር ያዘጋጀው አውደ ጥናት ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተጀምሯል። በዚህ ወቅት የእንስሳት መድኃኒት፣ መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጠርዙ ዳያ የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የሕብረተሰቡን ጤና ለማረጋገጥና የእንስሳት ውጤቶችን የወጭ ንግድ ለማበረታታት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ይህን እውን ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ በሽታ አምጪ ተዋሲያን ከመደኃኒት ጋር መላመድ በከፍተኛ ደረጃ መነቆ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰዋል። ዶክተር ጠርዙ እንዳሉት ለበሽታ አምጪ ተዋሲያን መከሰትና መድኃኒት መላመድ ከተለዩት ተግዳራቶች መካከል ልቅ ግጦሽ መስፋፋት፣ ያልተገደበ የእንስስት እንቅስቃሴ መኖር፣ የመድኃኒትና የእንስሳት መኖ ጥራት መጓደል ይገኙበታል። ከእዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ ሁለት የዝናብ ወቅቶች ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ ለበሽታ አምጪ ተዋሲያን መንሰራፋት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ጥራቱ፣ ደህንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድኃኒት ብቻ አገር ውስጥ እንዲገባ የላቦራቶሪ የቁጥጥር ሥርዓት አለመኖር ሌላው ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱንም ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። በጥናት በተለዩ ተግዳራቶች ላይ መግባባት ለመፍጠርና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ሲባል መድርኩ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል። በመድኃኒት አስመጪዎችና መኖ አቀነባባሪዎች፣ ክልል ተሻጋሪ ጅምላ አከፋፋዮች ላይ ተገቢ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ሙሉ ለሙሉ ጥራቱ የተረጋገጠ ምርት ብቻ አገር ውስጥ እንዲገባና ጥቅም ላይ እንዲውል ባለስልጣኑ ግብ ይዞ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።  ለዚህ ስኬት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ላቦራቶሪ ተገንብቶ ሥራ መጀመሩን ገልጸው ይህም ጥራቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድኃኒት ብቻ አገር ውስጥ እንዲገባ ምቹ ሁኔታእንደሚፈጥር አስረድተዋል። በዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት የድንበር ተሻጋሪ የእንስስት በሽታዎች አስቸኳይ ማዕከል ምክትል ቡድን መሪ ዶክተር ወንደወሰን አስፋው በበኩላቸው በሽታ አምጪ ተዋሲያን በዓለም ላይ ከፍትኛ ችግር እየፈጠሩ መምጣታቸውን ገልጸዋል። "በተለይ አዲስ የሚወጡ መድኃኒቶች አለመኖርና ያሉትም መድኃኒቶች ከበሽታ ጋር የመላመድ ባህሪ ማሳየታቸውን ግምት ውስጥ አስገብቶ ከወዲሁ የእንስሳት በሽታዎችን ለመቆጣጠር ካልተሳራ ችግሩ ከአቅም በላይ ሆኖ የሰውም የእንስሳትም ስጋት ይሆናል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ድርጅቱ እኤአ ከ2016 ጀምሮ ድንበር ተሻጋሪ የእንስሳት በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ፕሮግራምና ፕሮጀክት በመቅረጽ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ14 የአፍሪካ አገራትና በሌሎችም የእስያ አገሮች ውስጥ በመስራት እገዛ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል። ይህ እንቅስቃሴ በተለይ በአገሪቱ የሚከሰቱ ድንበር ዘለል በሽታዎችን አስቀድሞ የመከላከልም ሆነ ከተከሰተም በኋላ በፍጥነት በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያግዝ አመልክተዋል፡፡ "ይህም አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸውን እንስሳትም ሆነ የእንስሳት ውጤቶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲላኩ በማድረግ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያስችላታል" ብለዋል፡፡ ፀረ–ተዋሲያን በጀርሞች መላመድ አስመልክቶ ጥናት ያቀረቡት አቶ ጤናው አንዱአለም እንዳሉት በዚህ ዓመት በመላ ሀገሪቱ የተካሄደው ጥናት በመድኃኒት አያያዝና አጠቃቀም ምክንያት የፀረ–ተዋሲያን በጀርሞች የመላመድ ችግር እያጋጠመ ነው። ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከምርምር ተቋማትና ከሌሎችም አካላት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም