በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ 14 ሰዎች ለይቶ ማቆያ ማዕከል ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ 14 ሰዎች ለይቶ ማቆያ ማዕከል ገብተዋል
አዲስ አበባ ( ኢዜአ) ጥር 28/2012 በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ 14 ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ማዕከል መወሰዳቸውን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አስታወቀ። ኢንስቲትዩቱ የቫይረሱን ስርጭትና አዳዲስ መረጃዎች አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ 14 አዲስ በቫይረሱ የተጠረጠሩ ሰዎች በለይቶ ማቆያ ማዕከል ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጿል። የቫይረሱን ስርጭት የተመለከቱ 29 ጥቆማዎች ለኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል መድረሳቸውንም አስታውቋል። በጥቆማው መሰረት በተጠረጠሩ 29 ግለሰቦች ላይ በተደረገው ማጣራት 14ቱ የበሽታው ምልክቶች የታየባቸው በመሆኑ ኢንስቲትዩቱ በለይቶ ማቆያ ማዕከል ክትትል እንዲያደርጉ ወስኗል። 11 ናሙናዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልከው ስምንቱ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው መረጋገጡንም ጠቅሷል። የሶስት ናሙናዎች የምርመራው ውጤት እየተጠበቀ መሆኑን ያብራራው መግለጫው በቀጣዮቹ ሶስት ቀናት ደግሞ ሌሎች ሶስት ናሙናዎች ለምርመራ ይላካሉ ብሏል። በተጨማሪም ከቻይና ዉሃን ከተማ የሚመጡ ሁሉም መንገደኞች ለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲገቡ የተወሰነ ሲሆን በማዕከሉ ውስጥ ሆነው አስፈላጊው የሕክምና ክትትል እንደሚደረግላቸው ተገልጿል። በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከቻይና የሚመጡ መንገደኞች ከሌሎች መንገደኞች ጋር ሳይቀላቀሉ የሙቀት መጠን ምርመራ እየተደረገላቸው መሆኑን መግለጫው አትቷል። ከቻይና ለሚመጡ መንገደኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ የኢሚግሬሽን ልዩ መስኮትም ተዘጋጅቷል፡፡ ከቻይና የሚመጡ መንገደኞችን የጤና ሁኔታ መከታተል እንዲቻል ለባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቶ አገልግሎቱ መጀመሩን ያብራራው መግለጫው በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ለሚሰሩ ሁሉም አካላት በበሽታው ዙሪያ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎችን በሚመለከት ስልጠና እየተሰጣቸው ነው ተብሏል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ከታየባቸው አገራት የመጡ መንገደኞች ወይም በቫይረሱ ከተያዙ ግለሰቦች ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ላይ የበሽታው ምልክቶች ማለትም ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥና የመተንፈስ ችግር ከታየ ማንኛውም ሰው በአስቸኳይ በ8335 ነጻ የስልክ መስመር በመደወል ሪፖርት እንዲያደርግ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል፡፡ የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች ሲያስነጥሱና ሲያስሉ አፍና አፍንጫቸውን በሶፍት ወይም በክርን እንዲሸፍኑ፣ የተጠቀሙበትን ሶፍት እንዲያቃጥሉ እንዲሁም እጃቸውን በሳሙና በመታጠብ የቫይረሱን ስርጭት መከላከል እንደሚገባም ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም ኅብረተሰቡ በአገሪቷ እስካሁን በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠ ሰው አለመኖሩን አውቆ ሳይዘናጋ የበለጠ ጥንቃቄ ኢንዲያደርግም ኢንስቲትዩቱ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ31 ሺህ በላይ ሲሆን 636 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል፡፡