ቀጥታ፡

የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ይገባሉ

አዲስ አበባ ፣ጥር 29/2012 (ኢዜአ) የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ይገባሉ።

ትሩዶ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ለኢዜአ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውይይታቸው በተጨማሪ በነገው የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ስብስባ ላይ እንደሚታደሙም ታውቋል።

በተጨማሪም የካቲት 1 እና 2 ቀን 2012 ዓ.ም በሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ለመታደም የአፍሪካ አገራት መሪዎች ከዛሬ ጀምሮ አዲስ አበባ እንደሚገቡም አቶ ነቢያት ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ሴኔጋልንና ጀርመንን እንደሚጎበኙ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ባሉ የኢኮኖሚ አማራጮች፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በዲሞክራሲና በጾታ እኩልነት ላይ እንደሚወያዩም ተገልጿል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የካናዳ አነስተኛ ንግድ የወጪ ንግድ ማስፋፊያና አለም አቀፍ ንግድ ሚኒስትር የሆኑት ወይዘሮ ሜሪናግ አብረዋቸው እንደሚመጡ ከዚህ ቀደም መገለጹ ይታወሳል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ጉብኝት በሁለቱ አገራት መካካል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት በሚያሳድጉበት ሁኔታ ለመምከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተገልጿል።

ኢትዮጵያና ካናዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.አ.አ በ1965 የጀመሩ ሲሆን በቀጠናው ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ የንግድ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትበብራቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን መረጃች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም