ቀጥታ፡

የኮሮና ቫይረስን ለመቆጣጠር የአባል አገራትን አቅም ለመገንባት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 29/2012 (ኢዜአ) የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል የኮሮና ቫይረስ አፍሪካ እንዳይገባና ከገባም በኋላ ሥርጭቱን ለመግታት ከአባል አገራት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ማዕከሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ምክንያት በማድረግ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ ማቋረጣታቸው ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ገልጿል። የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል ዳይሬክተር ጆን ንኬንጋሶንግ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እስካሁን በቫይረሱ የተጠቃ አንድም ግለሰብ አለመኖሩን አረጋገጠዋል። ይሁን እንጂ በሁሉም የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት ቫይረሱ ወደ አገራቸው እንዳይገባና ምናልባትም ቢገባ በምን መልኩ መቆጣጠር እንደሚገባ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይም ወደ ቻይና ቀጥታ በረራ ያላቸው አንዳንድ የአፍሪካ አገራት በረራ ማቆማቸውን ገልጸው ይህ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነና ትክክለኛው መንገድ ጥንቃቄ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል የዓለም የጤና ድርጅት ያወጣውን 'በረራ መቆም የለበትም' የሚለውን አቋም በተመሳሳይ እንደሚከተል ነው ያረጋገጡት። ስለዚህም ወደ ቻይና በረራ የሚያደርጉ አገራት ብቻ ሳይሆን ሁሉም አገራት ለቫይረሱ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁመው በአህጉር ደረጃ ሁሉን አቀፍ 'አምስት ሥራዎች' እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል። ማዕከሉ በመጀመሪያ ደረጃ ከሚያከናውነው የሥልጠና መርኃ ግብር ውስጥ በአንደኛው ዙር ከ15 አገራት የተውጣጡ 15 የጤና ባለሙያዎች በቤተ-ሙከራ ሥልጠና እየወሰዱ መሆኑን አስረድተዋል። በሁለተኛ ዙር ደግሞ 20 የጤና ባለሙያዎች ከ20 አገራት እንደሚሳተፉ ጠቁመው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሁሉም የአፍሪካ አባል አገራት የተውጣጡ ባለሙያዎች ሥልጠናውን ይወስዳሉ ብለዋል። በቅርቡ ደግሞ በአየር መንገዶች አካባቢ የሚደረገውን የምረመራ ሥራ በጥራትና ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኋን እንዲተገበር ለማስቻል የሚያግዝ ሥልጠና እንደሚጀመር ተናግረዋል። እነዚም ሥልጠናዎች የኮሮና ቫይረስ ወደ አፍሪካ እንዳይገባ፤ ከገባም በኋላ በተሳካ መልኩ ሕክምና በመስጠት የቫይረሱን ሥርጭት በእንጭጩ ለመቆጣጠር እንደሚረዱ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ያም ሆኖ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ፈጣን መሆኑን አንስተው አፍሪካዊያኖች ቫይረሱን በቀላሉ ለመከላከል የግል ንጽህናን መጠበቅ አንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት። በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ዜጎች ቁጥር ከ31 ሺህ በላይ ሲሆን፤ የሞቱ ሰዎች ቁጥርም ከ600 በላይ ደርሷል። አብዛኛውን አሃዝ የምትይዘው ቻይና ናት። በአሁኑ ወቅት ከቻይና ውጭ በፊሊፒንስ በኮሮና ቫይረስ የሞተ ሰው የተመዘገበ ሲሆን ቻይናን ጨምሮ በ23 አገራት ላይ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ግለሰቦች ተገኝተዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም