ቀጥታ፡

የገናሌ ዳዋ የኤሌክትሪክ ኋይል ማመንጫ ፕሮጀክት መገንባት የመሰረተ ልማት ችግርን ፈቶልናል--ነዋሪዎች

አዲስ አበባ ጥር 28/2012 (ኢዜአ) የገናሌ ዳዋ 3 የኤሌክትሪክ ኋይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአካባቢያቸው በመገንባቱ የመሰረተ ልማት ችግሮቻቸውን እንደተቃለሉላቸው ፕሮጀክቱ የሚገኝበት የባሌና ጉጂ አካባቢ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ በፕሮጀክቱ የመስኖ ልማት ለማካሄድ ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል። ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የባሌና የጉጂ ዞኖች ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ በመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታ ወደ ኋላ የቀረውን አካባቢ ቀይሮታል። ፕሮጀክቱን ተከትሎ የጠጠር መንገድ ያልነበረው አካባቢው አስፓልት መንገድ መቻሉን ገልጸው፤ ''ከመንገድ በተጨማሪ የአሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነናል'' ብለዋል። የማህበረሰቡን ማህበራዊ ጫና ማቃለል የሚችሉ መሰረተ ልማቶች ተጠቃሚ ለመሆን መብቃታቸውን የተናገሩት አቶ አብዲ ሀጂ ሁሴን የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ፤ ፕሮጀክቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይዞ እንደመጣ አመልክተዋል። አቶ ሁሴን ዌቦ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው ''በወንዝ መኖር የተነሳ በበጋ ወቅት ብቻ ተወስኖ የቆየው የወንዝ ማዶ ማህበረሰቦች ግንኙነት በድልድይ መገንባት ምክንያት በጋ ከክረምት ሆኗል'' ብለዋል። አካባቢው የነበረው አስፈሪ ገጽታ ተቀይሮ እንደልብ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ለመሆን መብቃቱን ተናግረዋል። ቀደም ሲል ለአገልግሎት መብቃት ያልቻለው አካባቢ በግድቡ ፕሮጀክት መልማቱን የገለጹት አቶ ከሊፍ ሁሴን፤ ''ፕሮጀክቱ በመጀመሪያ የአካባቢውን ኅብረተሰብ ተጠቃሚ በማድረጉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ለኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫነት የተገደበው ውሃ ህብረተሰቡ ለመስኖ ልማት እንዲያውለው መንግሥት በማህበር አደራጅቶ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የገናሌ ዳዋ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ቴዎድሮስ ሁሴን በሰጡት አስተያየትም በፕሮጀክቱ ምክንያት የአካባቢው ኅብረተሰብ በመሰረተ ልማት መጠቀሙን አረጋግጠዋል፡፡ በባሌና ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ የሚገኘው የገናሌ ዳዋ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 254 ሜጋዋት የማመንጨት አቅም አለው፡፡ ለፕሮጀክቱ 451 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል። የፕሮጀክቱ የአገሪቱን ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅምን ወደ 4ሺህ 654 ሜጋ ዋት ከፍ እንዳደረገው ታውቋል፡፡ የገናሌ ዳዋ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ጥር 26 ቀን 2012 በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መመረቁ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም