ቀጥታ፡

ጥንቃቄ የጎደለው የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ በሰውና እንሰሳት ላይ ጉዳት እያስከተለ ነው- የከተሞች ነዋሪዎች

ጎንደር ኢዜአ ጥር 28 /2012 ዓ.ም ጥንቃቄ የጎደለው የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ አካባቢን በመበከል በሰውና እንሰሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን በምዕራብ ጎንደር ዞን የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ገለፁ። ችግሩን በጊዜያዊና ቋሚነት ለመፍታት ከከተሞች ማዘጋጃ ቤቶች ጋር እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል። የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪ አቶ ሰጠኝ ካሴ ለኢዜአ እንደገለፁት በግዴለሽነት የሚወገድ ደረቅ ቆሻሻ ከተማውን በሚያቋርጡ የገንዳ ውሃና ሆርሸዲ ወንዞች ላይ ብክለት እያስከተሉ ነው። ወንዞቹ ውስጥ ያለገደብ እየተጣለ ያለው ቆሻሻ በእንስሳትና በሰዎች ጤና ላይ ጉዳት እያደረሰ መምጣቱን ጠቁመዋል ። "በግዴለሽነት የሚወገድ የደረቅ ቆሻሻ ወንዞችን ከመበከል ባለፈ በከተማው ዙሪያ ባሉ የእርሻ መሬቶች ላይ ጉዳት እያስከተለ ነው" ያሉት ደግሞ በመተማ ወረዳ የኮኪት ከተማ ነዋሪ አቶ መሐመድ ለጋስ ናቸው። በከተማው የተቋቋሙ የፅዳት ማህበራት ከመኖሪያ ቤቶችና ከድርጅቶች የሚወጡ ደረቅ ቆሻሻዎችን በመሰብሰብ ዙሪያውን በሚገኙ የእርሻ ይዞታዎች ላይ እንደሚደፉ ተናግረዋል። "የእርሻ ማሳየን በፕላስቲክ ቆሻሻ በመሞላቱ ለምነቱን እያጣ ነው" ያሉት አቶ መሀመድ ከማሳው ላይ የሚያገኙት የሰብል ምርት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሆኑን ገልፀዋል ። በቋራ ወረዳ የገለጉ ከተማ ነዋሪ አቶ ጥላሁን እያዩ በበኩላቸው ከከተማው የሚሰበሰብ ደረቅ ቆሻሻ በወንዞችና እርሻ ማሳዎች ዳርቻ ላይ ስለሚወገድ የአካባቢ ብክለት እያስከተለ መሆኑን ጠቁመዋል ። በከተማው ዙሪያ ያሉ ወንዞችና የእርሻ ማሳዎች በታሸጉ የውሃና የለስላሳ መጠጦች መጠቀሚያ ፕላስቲኮች መሞላታቸውን ተናግረዋል ። የእርሻ ማሳ ውስጥና ዳርሻዎች በፕላስቲክ ቆሻሻ መሞላታቸው በእንስሳት ግጦሽ ሳር ላይ እየደረሰ ካለው ጉዳት በተጨማሪ ማሳዎች የአፈር ለምነታቸውን እያጡ መጥተዋል ። በአካባቢው የሚገኘው የለገለጉ ወንዝ በፕላስቲክ ቆሻሻ በመሞላቱ በውስጡ ያለው የዓሳ ሀብት እየተመናመነና እየጠፋ መምጣቱንም ነዋሪው ተናግረዋል። በገንዳ ውኃ ከተማ የደረቅ ቆሻሻ አስወጋጅ ማህበራት ሰብሳቢ አቶ አለምነው ሲሳይ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት ከተማው እራሱን የቻለ የቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራ ስለሌለው የሚሰበሰቡ ቆሻሻዎች ከከተማው ወጣ ባሉ አካባቢዎች እንደሚደፉ ተናግረዋል ። "ፕላስቲክን ጨምሮ የደረቅ ቆሻሻ በንፋስ ኃይል ወደ ወንዝና የእርሻ መሬቶች ስለሚበተን ችግሩ አባብሶታል "ብለዋል። ግለሰቦችም ከመኖሪያ ቤታቸው  የሚወጡ ቆሻሻዎችን በቀጥታ በወንዝ ውስጥ መጣላቸው ሌላው ምክንያት በመሆኑ የከተማው አገልግሎት ጽህፈት ቤት ጉዳዩን እንዲያውቀው መደረጉን አቶ አለምነው ተናግረዋል። በገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር የአገልግሎት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም ኢብራሂም በበኩላቸው በከተማው አግባብ ያለው የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ እንዲኖር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የፅዳትና ውበት አደረጃጀትን የማጠናከርና የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ መረጣ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል። በከተማው በወንዝ ዳርቻዎችና የእርሻ ቦታዎች የሚጣሉ ቆሻሻዎችን ለመከላከል የሚደረገውን ስራ የሚያግዝ የቅጣት ደንብ በከተማ ምክር ቤት ለማጽደቅ እየተሰራ መሆኑን አቶ አብዱልከሪም አስታውቀዋል። የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና ልማት መምሪያ የአካባቢ ህግ ተከባሪነትና ማህበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ አድጎ በበኩላቸው በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር ወንዞችና የእርሻ መሬቶች ብክለት እያጋጠማቸው መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም በቀጥታ ከሱዳን ያለገደብ የሚገቡ የታሸጉ የፕላስቲክ መጠጦችና ምርቶች በአካባቢው ገበያ ስለሚውሉ ችግሩን ያባባሰው መሆኑን ጠቅሰዋል ። በአመት ከ4 ቶን በላይ የፕላስቲክ ቆሻሻ በዞኑ ባሉ ከተሞች ያለአግባብ እንደሚወገድ በቅርቡ በተካሄደ ጥናት መረጋገጡን ለአብነት ጠቅሰዋል ። በከተሞቹ ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት በመተግበር ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በየከተሞቹ ካሉ የማዘጋጃ ቤቶች ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል ። ከተሞቹ የቆሻሻ አወጋገድ አስተዳደርና ስርዓታቸውን እንዲያሻሽሉና እራሱን የቻለ የቆሻሻ ማስወገጃ እንዲያዘጋጁ አቅጣጫ መቀመጡንም ጠቅሰዋል ። እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ በየከተሞቹ የተደራጁ የደረቅ ቆሻሻ አስወጋጅ ማህበራትን የማጠናከር፣ የመደገፍና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎችም እየተከናወኑ ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም