ማይጨው፣ ጥር 28/2012 (ኢዜአ) የታዋቂው አትሌት አባዲ ሀዲስ የቀብር ስነ ስርዓት በእንዳመሆኒ ወረዳ ሰረንጋ በተባለ የትውልድ ስፍራው ዛሬ ተፈፀመ። ባደረበት ህመም ምክንያት ከትናንት በስቲያ ከዚህ አለም በሞት የተለየው የአትሌት አባዲ ሀዲስ የቀብር ስነስርዓት ቤተሰቦቹ ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ በተገኙበት በሰረንጋ ቅዱስ ስላሴ በቴክርስትያን ተፈፅሟል። በቀብር ስርዓቱ ላይ አትሌት ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ አመራሮችና የትግራይ ደቡባዊ ዞን መስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ተገኝተው ሃዘናቸውን ገልፀዋል። የአትሌት አባዲ ሀዲስ ሕይወት ታሪክ እንደሚያስረዳው ከእናቱ ከወይዘሮ ሰውየ ሐጎስ እና ከአባቱ አቶ ሀዲስ እምባየ በ1990 ዓ.ም በትግራይ ደቡባዊ ዞን እንዳመሆኒ ወረዳ ስምረት ቀበሌ ሰረንጋ በተባለው መንደር ተወልዷል። እድሜው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በሰረንጋ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በማይጨው ከተማ በጥላሁን ይግዛው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መከታተሉን የህይወት ታሪኩ ያስረዳል። ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በእንዳመሆኒ የአትሌቲክሰ ማሰልጠኛ ጣቢያ የአትሌቲክስ ህይወቱን የጀመረው አትሌት አባዲ ሀዲስ ጥሩ ብቃት በማሳየቱ በ2005 ዓ.ም ለማይጨው አትሌቲክሰ ማሰልጠኛ ማዕከል መመረጥ ችሏል። ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ትራንስ ኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ክለብ በመቀላቀል ሕይወቱ እስካለፈበት ዕለት ድረስ በተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች በመሳተፍ ክለቡንና ሀገሩን ማስጠራት የቻለ ታላቅ አትሌት ነበር። በ5 ሺህ ፣ በ10 ሺህ ሜትርና በግማሽ ማራቶን ተወዳዳሪ የነበረው አትሌት አባዲ ሀዲስ በ2016 በብራዚል በተካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር፣ በ2017 በለንደን በተካሄደው የዓለም አትሌትክስ ሻምፒዮና እንዲሁም በ2019 በዶኻ ኳታር በተካሄደው የ2019 የዓለም አትሌቲክሰ ሻምፒዮና በመሳተፍ ኢትዮጵያን አስጠርቶ ነበር ። በአህጉር አቀፍ ደረጃም በኡጋንዳ ካምፓላ በ2017 በተካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር የነሃስ ሜዳልያ አግኝቷል፡፡ አትሌት አባዲ ሀዲስ በህመም ምክንያት ለሶስት ወራት ያህል ህክምና ሲከታተል ቆይቶ ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት ላይ በ22 ዓመቱ በመቀሌ ዓይደር ሆስፒታል ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
 |
|