በድሬዳዋ የተገነባ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቃ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ የተገነባ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቃ
ድሬዳዋ፣ ጥር 28/2012 (ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር ለገኦዳ ገጠር ቀበሌ 35 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተገነባ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቃ፡፡ በአስተዳደሩ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት የ"ዋን ዋሽ " መርሃ ግብር አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ከበደ እንዳሉት ከ37 ኪሎ ሜትር በላይ የውሃ መስመር የተዘረጋለት ፕሮጀክት በታቀደለት አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቋል። 28 የውሃ ማደያዎችና እስከ 450 ሺህ ሜትር ኪዩብ መያዝ የሚችሉ የውሃ ማጠራቀሚያዎችን እንዳሉት ገልጸው ለቀበሌው ነዋሪዎች ለሚቀጥሉት 15 ዓመታት አገልግሎት መስጠት እንደሚችል አመልክተዋል። ፕሮጀክቱ ከፀሃይ ኃይል ኤሌክትሪክ ማግኘቱ በፍጥነት ወደ አገልግሎት እንዲገባ ማስቻሉን የተናገሩት አስተባባሪው "ቀበሌውን የመደበኛ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ እተከናወነ ይገኛል" ብለዋል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አህመድ ሰኢድ በበኩላቸው በ"ዋን ዋሽ " መርሃ ግብር የተገነባው ፕሮጀክት በታቀደው ጊዜና በጀት መጠናቀቁ ለሌሎች ቀጣይ ሥራዎች ልምድ የተገኘበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ይህንን መልካም ተሞክሮ በመጠቀም በፀኃይ ኃይል የሚሰሩ ተመሣሣይ የውሃ ፕሮጀክቶች በአርብቶ አደሩ ቀበሌዎች መገንባት መጀመሩንም ገልጸዋል። ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ኑሪያ ሃሚዶ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ለድሬዳዋ አስተዳደር ለዓመታት ሲያቀርቡት ለነበረው የንፁሁ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጥያቄ አሁን ምላሽ ማግኘታቸውን ገጸዋል። " ለስምንት ሰዓታት ከኩሬና ከወራጅ ወንዝ ውሃ ፍለጋ መንከራተት ቀርቶልናል ፤ ችግራችን ተፈቶልናል" ብለዋል፡፡ ወይዘሮ ከዶ ኑህ የውሃውን ደህንነት ለመጠበቅ ከቀበሌው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር የውሃ ቦኖዎቹን በራሳቸው ወጪ ማጠራቸውን ጠቁመው ሲበላሹም መጠገን እንዲቻል ኮሚቴ ማቋቋማቸወን ተናግረዋል፡፡ በአካባቢያቸው የነበረው የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር መፍትሄ በማግኘቱ የቀበሌው ነዋሪዎች መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ የቀበሌው ሊቀመንበር አቶ አልይ አህመድ ናቸው። የቀበሌው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር መሐመድ ሙሳ በበኩላቸው ከ1ሺህ በላይ ተማሪዎች እንዳሉ ገልጸው ተማሪዎች ውሃ ፍለጋ የትምህርት ጊዜያቸውን በማባከን በውጤታቸው ላይ ተጽዕኖ ሲያሳድር እንደነበር አስታውሰዋል። "አሁን ግን ችግሩ ሙሉ ለሙሉ መፈታቱ ለኛም፣ ለተማሪዎቹም፣ ለወላጆችም ትልቅ እፎይታ ነው" ብለዋል፡፡ በለገኦዳ ጉኑን ፈታ ጤና ጣቢያ አዋላጅ ባለሙያው ሲስተር ቤተልሄም ምትኩ ፕሮጀክቱ በህብረተሰቡ ላይ ሲደርሱ የነበሩ ውሃ ወለድ በሽታዎችን ለማስቀረት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።