ኢትዮጵያ በአፍሪካ የብልጽግና ደረጃ 41ኛ ላይ ትገኛለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የብልጽግና ደረጃ 41ኛ ላይ ትገኛለች
ጥር 28/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በብልጽግና 41ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ዓመታዊው የአፍሪካ የብልጽግና ሪፖርት አመላከተ። ዓመታዊው የአፍሪካ የብልጽግና ሪፖርት ዛሬ ይፋ ሆኗል። ሪፖርቱ እንዳመላከተው ኢትዮጵያ በብልጽግና 41ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን የጤና ስርዓቷን በማሻሻል ከአፍሪካ 21ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በትምህርት 29ኛ ደረጃን ስትይዝ ፤ አገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እየታዩባት መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል። ሪፖርቱ በኢትዮጵያና ኤርትራና መካከል ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የነበረው ግጭት አብቅቶ ወደ ሠላም መምጣት መቻሉን ለአብነት አንስቷል። ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ሠላም ሽልማት እንዲቀዳጁ ማድረጉንና፤ አሁን በአገሪቷ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እንዳሉ እንዲሁም በነፃነት የመናገርና መረጃ የማግኘት መብት እየተሻሻለ መምጣቱን አትቷል። ከሪፖርቱ የብልጽግና መለኪያ መስፈርቶች ፀጥታና ደህንነት፣ የግለሰብ ነፃነት፣ የመንግስት ተጠያቂነት፣ ማህበራዊ ካፒታል፣ ኢንቨስትመንት፣ የኢንተርፕራይዞች ልማት፣ የገበያ መሰረተ ልማት፣ የኢኮኖሚ ጥራት፣ ጤና፣ ትምህርት፣ የተፈጥሮ ጥበቃና የአኗኗር ዘይቤ የሚሉት የመገምገሚያ ነጥቦች ይገኙበታል። በዚህ መሰረትም ደቡብ አፍሪካ 1ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ሰሜን አፍሪካ 2ኛ ደረጃን ይዛለች። ምስራቅ አፍሪካ 3ኛ፣ ምዕራብ አፍሪካ 4ኛ፣ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና 5ኛ ደረጃን ሲይዙ መካከለኛው አፍሪካ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሪፖርቱ ከአፍሪካ ቀንድ ኢትዮጵያና ጅቡቲን ወደ ብልጽግና ሽግግር እያደረጉ ያሉ አገራት ብሎ ሲያስቀምጣቸው ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳንን በአደጋ ውስጥ ያሉ ብሏቸዋል። ጅቡቲ 19ኛ ደረጃን በመያዝ የአፍሪካ ቀንድ አንደኛ ስትሆን ኢትዮጵያ 41ኛ በመሆን ከቀጣናው 2ኛ ደረጃን አግኝታለች። ሱዳን 47ኛ፣ ደቡብ ሱዳን 54ኛ፣ ሶማሊያ 50ኛ ደረጃ ላይ ናቸው በሪፖርቱ። ከምስራቅ አፍሪካ ደግሞ ሩዋንዳ 11ኛ፣ ኬንያ 15ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አንፃራዊ የሆነ ዝቅተኛ የሙስና መጠን፣ ዝቅተኛ የወንጀል ሪፖርቶችና በጤናው መስክ እየታየ ያለው መሻሻል የአፍሪካ ቀንድ አገራት ጥንካሬ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል። የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ቀንድ ጎረቤት አገራትን ለማስተሳሰር የሚያደርገው ጥረትና ትምህርት እንደ ሌሎቹ የአፍሪካ አገራት እየተስፋፋ መምጣቱን ሪፖርቱ እንደ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ተመልክቶቷል። በቀጣናው የአንዳንድ አገራት የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ ጦርነትና ከሌሎች የአፍሪካ አገራት አንፃር በፀጥታና ደህንነት ረገድ እንደ ድክመት ተመልክቶታል። ድርቅ ለቀጣናው የውሃ ሀብትና የምግብ እጥረት ቀጣይ ፈተና ሊሆን ይችላል ሲልም አመላክቷል። ሪፖርቱ የወጣው ሌጋቶም እና ሆርን ኢኮኖሚክ ኤንድ ሶሻል ፖሊሲ በተሰኙ ኢንስቲትዩቶች ነው።