የቁም እንስሳት ኮንትሮባንድ ንግድ ለስርቆት መንስኤ እየሆነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቁም እንስሳት ኮንትሮባንድ ንግድ ለስርቆት መንስኤ እየሆነ ነው

ጎንደር፣ ጥር 28/2012 (ኢዜአ) በምእራብ ጎንደር ዞን ህገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድን ተከትሎ የከብቶች ስርቆት እየተስፋፋ በመምጣቱ መቸገራቸውን የዞኑ ከፊል አርብቶ አደሮች ገለፁ። በቁም እንስሳት የሚካሄድ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል ኬላዎችን የማጠናከር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ የዞኑ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ አስታውቋል። በዞኑ የቋራ ወረዳ ነዋሪ አቶ ስጦታው አማረ ለኢዜአ እንደገለጹት በወረዳው ነብስ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የቁም እንስሳት ኮንትሮባንድ ንግድ ይካሄዳል። ይህንኑ ተከትሎ ባለፈው ህዳር ወር 10 ቁም ከብቶቻቸው ተሰርቀው ወደ ሱዳን በኮንትሮባንድ ንግድ በመሻገራቸው ከብቶችን ፈልገው ለማግኘትም ሆነ ወንጀለኞችን ለማስያዝ አዳጋች እንደሆነባቸው ገልጸዋል። የመተማ ወረዳ ነዋሪና ከፊል አርብቶ አደር አቶ ሰዒድ ሀሰን ባለፈው መስከረም ወር 23 በጎችና 10 በሬዎች እንደተሰረቁባቸው ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ በአካባቢው በተደጋጋሚ በሚፈጸመው የእንስሳት ስርቆትና ዘረፋ ምክንያት ከብቶቻቸውን ለጠበቂ ሰጥተው ሌላ ስራ ለማከናወን መቸገራቸውን ገለጸዋል። ከፊል አርብቶ አደር አቶ ማሙየ መንግስቱ በበኩላቸው በመተማ በኩል ወደ ሱዳን በሚደረገው የቁም እንስሳት ኮንትሮባንድ ንግድ ምክንያት ከብቶቻቸው በተደጋጋሚ እንደሚሰረቁ አውስተዋል። በመስከረም ወር ብቻ አምስት በሬዎቻቸው ተሰርቀው ወደ ሱዳን በኮንትሮባንድ ንግድ መሻገራቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል። መንግስት ችግሩን በመገንዘብ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ከፊል አርብቶ አደሮቹ ጠይቀዋል። በምዕራብ ጎንደር ዞን የንገድና ኢንዱስትሪ ገበያ ልማት መምሪያ የግብይት ዋና ቡድን መሪ አቶ ክብረት ሙጬ በጉዳዩ ዙርያ በሰጡት አስተያየት የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል ኬላዎችን የማጠናከር ስራ እየተካሔደ ነው። ይሁን እንጂ ወደ ሱዳን የሚካሄደውን የቁም እንስሳት የኮንትሮባንድ ንግድ በዋና ዋና መተላለፊያ መንገዶች ጥብቅ ቁጥጥር ሲደረግ በጫካ በኩል ሌላ መተላለፊያ መንገድ በመፍጠር ችግሩን ለማስቆም የሚደረገው ጥረት አዳጋች እንዳደረገው ተናግረዋል። ሁኔታው የእንስሳት ስርቆት እንዲስፋፋና ሀገሪቱም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንድታጣ ማድረጉን አስረድተዋል። ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በተደረገ ጥረትም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሱዳን ሊሻገሩ የነበሩ 69 የቀንድ ከብቶች ተይዘው በውርስ ለመንግስት ገቢ መደረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ በዓመት ከ40 ሺህ በላይ የቁም እንስሳት በኮንትሮባንድ መልኩ ወደ ሱዳን እንደሚሻገር ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል። በዞኑ ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ የቁም እንስሳት ሀብት አለ ተብሏል።